ጉዞ ሰውና ዝንጀሮ በቃል ኪዳን ወደሚኖርበት ተራራ


(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከላሊበላ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ከሚባሉት አንዱን ወጥቶ ሰው እና ዝንጀሮ በቃል ኪዳን የሚኖርበት ምድር ነኝ ሲል አስደናቂውን ተፈጥሮ እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡)

482580_511500905566432_536732242_n.jpg

Lalibela Hudad, a lodge for trecking to Abune Yosef

ሰው እንዴት ላሊበላ መጥቶ እዚህ ሳይደርስ ይመለሳል? እውነቴን ነው የምነግራችሁ እጅግ አስደናቂ በሆነው የሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ተራራ ላይ ነኝ፡፡ በቀጠናው ከሚገኙ ከፍታዎች እዚህ ላይ የሚደርስ የለም፡፡ እዚህ ሁሉም ቁልቁል ናቸው፡፡ አደፋን አዘቅዝቄ እያየኋት ነው፡፡

የተነሳሁት ከደብረ ሮሐ ላሊበላ ከተማ ነው፡፡ ከቅድስቲቷ መዲና፤ አርባ ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዤ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ አቤት ተፈጥሮ…..አቡነ ዮሴፍ ጥብቅ ስፍራ ሲባል ከሰማችሁ ይሄ ነው፡፡ የፍራንክፈርት ዙ ኦሎጂካል ሶሳይቲ ባለሙያዎች ድካም እውን ያደረገው ድንቅ ተፈጥሮ፤ እዚህ ስለ ቀይ ቀበሮ ህልውና እነኚህን ተራሮች ብዙዎች ወጥተው ወርደው፤ ጭላዳን ምቹ ሀገር እንዲኖረው የባተሉ የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ብዙ ናቸው፡፡

በሀገራችን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፤ አቡነ ዩሴፍ፤ ትልቁን ተራራ እየወጣሁ ነው፡፡ ቀኑ እኩል ሆኗል፡፡ ሪም ገደል ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ በበረዶ ተሸፍኗል፡፡ ጅብራ እዚያም እዚህም ይታያል፡፡ ሪም ገደል በኢትዮጵያ ሶስተኛው ተራራ ነው፡፡ ከስሜን ተራሮች እና ከቱሉ ዲምቱ ቀጥሎ ወደ አናቱ እየወጣን ነው፡፡ ድንጋይ እየቧጠጥን በረዶ እያንሸራተተን፡፡

15207976_1184021031645216_75462048_n.jpgአሁን 4284 ሜትር ከፍታ ያለው አናት ላይ ወጣን፡፡ ቁልቁል ላስታ ነው፡፡ የዋግ ምድር ተንጣሎ ይታያል፡፡ እመኪና ሲባል ከሰማችሁ አሁን ከርቀት የማየው ተራራ ነው፡፡ ከአሸተን እስከ ቆቦ ከሪም ገደል አናት ፍንትው ብለው ይታያሉ፡፡

አቡነ ዩሴፍ ደብር ከስር ነው፡፡ የሥነ ምህዳሩ ስያሜ መነሾውም ይህ ስፍራ ነው፡፡ አቡነ ዮሴፍ አንድ ወቅት እዚህ ስፍራ የነበሩ መነኩሴ ናቸው፡፡ የበቁ አባት፡፡ ሰው ከዝንጀሮ ጋር ሲጣላ፣ ዝንጀሮ ማሳ ሲያወድም አይተው ያስማሙ፡፡ ዝንጀሮ ዳርቻው ላይ እየጨፈረ ግን የማይደፍረው ማሳ ብዙ ነው፡፡

ይሄ የስምምነታችው ውጤት ነው፡፡ አቡነ ዮሴፍ የአካባቢውን ሰው ከዝንጀሮ ጋር አስማሙ ህዝቡ ቃርሚያ ለዝንጀሮው ሊለቅ፣ ዝንጀሮው ማሳ ገብቶ ላያወድም፡፡ ከአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ዝንጀሮ ማሳውን የማይበላበት ገበሬ ሀገር የሆነው ምድር አናት ላይ ነኝ፡፡

ከስሜን የጀመረው የኢትዮጵያ ተራሮች ሥነ ምህዳር እዚህ ድረስ አካሉን ዘርግቷል፡፡ እነ ሀብታሙን የሚፈትኑ የላስታ ተራሮች ንጉሳቸው አቡነ ዮሴፍ ነው፡፡ የተከዜ ወንዝ ምንጭ የአቡነ ዮሴፍ ሥነ-ምህዳር ነው፡፡ አየሩ እጅግ ይቀዘቅዛል፡፡ ቁልቁል እየወረድን ነው፡፡ ከዚያ ዳግም ወደ አሽተን እንወጣለን፡፡

From:- DireTube News via News.et

please enter a message