አድዋ የማን


( ሄኖክ የሺጥላ )min

ዳግማዊ ሚኒሊክ በእንጦጦ ማሪያም በኣቡነ ማቲያስ ኣንጋሽነት በመስከረም ፪፩ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሁለት ኣመተ
ምህረት የንጉሰ ነገስትነት ዘውዳቸውን መጫናቸውን ተከትሎ ለተለያዩ ኣውሮጳ ሃገሮች ለጻፉት ደብዳቤ የመጣለቸውን
መልስ እያሰላሰሉ ከዙፋናቸው ላይ ቁጭ ብለዋል። ንዴታቸው ግን ፊታቸው ላይ ኣይታይም።የታላቋ ብሪታንያና የጀርመን
መንግስታቶች የጃንሆይን መልእክት ተከትሎ በጻፉት ደብዳቤ
ሚኒሊክ ንግስናዋን ከርሶ በቀጥታ ሳይሆን ወኪሎ ኢንዲሆን በፈቀዱት በጣልያንና በመንግስቱዋ በኩል ነው መስማት
ያለብን የሚለው ነገር ፤ የንጉሱን ባለሙዋለች እጅጉን ያበሳጨ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን እቴጌይቱን ነበር
ያስቆጣው።
እቴጌ ጣይቱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገሮች ጋር የሚኖራትን ግንኙንት በኢጣልያን በኩል ታደርካለች የሚለው የጣልያንኛው
ድብቅ የኣተረጉዋጎም ሴራ ፤ ኣዋ የውጫሌ ውሉ፤ ከውሉም የ ፩፯ኛው ኣንቀጽ ፤ ብሎም ንጉስ ምኒሊክ እንዲስማሙ
ላማድረግ ተብሎ ከጣልያን መንግስት ከንጉስ ኡምቤርቶ የቀረበው የሊሬና የ መሳሪያ እርዳታ ንዴታቸውን ከሚቆጣጠሩት
በላይ ገፍው። እቴጌይቱ በርጋታ ከተቀመጡበት ብድግ ኣሉ

የለም በለው!
ስጦታህ የምድርን ኣሸዋ ቢያጥፍ
ኣልፍ ሆኖ ለትውልድ ቢተርፍ ዕንኳ
የለም በልው
የለም የሚነጠቅ መሬት

እንኳንስ ቆርሼ የምሰጣቸው ምድር
እንኳንስ ኣሳልፈን የምንሰጣቸው ክብር
እንኵዋንስ የሚይስተዳድሩልን ሃገር
እንኳንስ የሚጠብቁልን ድንበር
በጫማቸው ጥርስ ይዘው የሚሄዱት እፍኝ ኣፈር የለንም

ስትለው
ያይንህ ጭራ ላይ ያለው ብናኝ ኣቡዋራ ኢንኳ የኔ ከሆነ ታጥበህ ነው የምሄደው
ጥፍርህ ውስጥ ያልው ጭቃ
በሰበዝ ተፍቆ እንደመጣሀው ነው የምንመልስህ
ብላሃለች ጣይቱ በልው፦

ምን ኣለ ነው ያልከኝ
ብረት ልስጥህ ሃገር ስጠኝ
ባሩድ ልስጥህ ኣፈር ስጠኝ
እንዲያ የሚል መልክት ነው ያገደመው
እንደዚያ ነው ኣለ ያልከኝ

ንገረው ብረት ቀለቤ ኣይደለም በልው
ኣስረግጠክ በለው ኣረር ኣረር የልፍኜ ፍሪዳ ኣይደለም በልው

ይሄን የጣይቱን ሃገር
ጋሻውን ያነገተው
የጦሩን ቻፍ ያነጠረው
ጦሩን ያጠነከረው በረት ኣይደለም በለው
ንገረው
ኣንጥረኛው ከቅዳሴ መልሰ ወናፉን የነፋው ባህታዊው ነው በለው
ማህሌት ባደረሰበት ድምጹ
እጣን መቅደስ ባጠነበት ገጹ
በበረከቱ ነው የጦሩን ብረት ያቀለጠው
ዕና ንገረው
ጦሬ ጫፍ ቅዳሴ ነው መለከት ነው በለው
በረከት ነው በለው
እንጂ ሃገሬ በሮማ ኣንጥረኛ
በነጭ በረኛ
ባንተ ብረት ማገርዋ ኣይጠብቅም
ባንተ ችሮታ ይህ የጥቁር ታቦት ኣይጠበቅም በለው

ተሳስተሃል በለው

የዘንዶ ጉድጉዋድ በሞኝ እጅ ይለካል ኣሉ
ባንተ ብረት ባንተ ንዋይ የኔን የጣይቱን ቤት መለካት ሽተህ ከሆነ
የያዘህ ይለቕ ዘንድ
የጦር መስቀል ደረት፤ህ ላይ ተክሎ
ፋኖ የሚል ባህት ኣለ
ና ሞክረኝ እዚህም ወንድ ኣለ፦

ምን ኣለ ነው ያልከኝ

ጥይት ሲጭሩት እሳት ይሆናል
ኣናውቅ መስሎህ ከሆነ እናውቃለን
ግን መተኮስ ብቻውን ድል ኣይሆንም
እርግጥ ነው እናንተ ጋ ጥይት ኣለ በለው
ግና እኔ ሃገር ወንድ ኣለ
እምቢ ያለ
ኣብራርተህ ንገረው
የሃር ኒሻን ደረቱ ላይ የከመረ የነጭ ግራዝማች
በጥጥ ቦላሌ
በባዶ እግሩ በሚሄድ
ኣባቱ ቁዋርፍ እያበላ ባሳደገው
ባፈር ባህታዊ ድል ይሆናል በለው

ንገረው፦

ስትለው ይሄ ኢትዮጵያ ነው በለው
ኢንጂ ብረት ተቀብለን
እራሳችኑ ላይ ጥግ ጥጉን መርተን
ያድዋ መቅደላ ዛሬ ኣናደርስ፡ህ፣ም በለው
የወጣኸውን ኣቀበት ኣትወርደውም በለው

ይሄ የኔ ኣፈር ነው
ይሄ የኔ ሃገር ነው
ይሄ የኔ ኣድባር ነው
ይሄ የኔ ኣውጋር ነው
ድግርና ሞፈሩ
ወጋግራና ኣጥሩ
ሲሻው በሾህ ሲሻው ባጋም
ሲሻው በኮሸም ቢታጠር
ጌሾ ቀበሪቾ ዝባድ ወይ ነጭ ዕጣን
ብሰነጥቅ ብፍቅ ባግት

ባገሬ ነው ሃገሬ ነው በለው
ኣንተ ምን ፈልገህ እዚህ መጣህ በልው፧
ሰሙ ጃንሆይ ሰሙ ጉዶትን
ምን ይጠብቃሉ ታዲያ ጣልያን ላማልዶ ሲሎ
እኔ እመ ብርሃን ልሆኖ ሲሎ ምን ይጠብቃሉ
እውር ኖት የሚያደርጉትን ኣያውቁም እኔ ኣፈ ሹም ልሆኖ
በኔ ኣንቀልባ ይዋሉ ነው እኮ የሚላ
ሲያሞ እኔ ታመሙ ልበል እኮ ነው የሚል
ሲያርሱ፤ ሲባዝቱ ሲጎለጉሉ፤ ለኔ ነግረው ይሁን እኮ ነው የሚል
ውሎ ኣድሮ ኣስፈቅደው እንዲተኙ፤ ኣስፈቅደው እንዲነሱ፤ ኣስፈቅደው እንዲወጡ፤ ኢንዲገቡ በኔ ብቻ ይሁን ነው እኮ የሚል
ምን ኣለ ነው ያልከኝ
ኣፈር ስጠኝ ሃግር ልስጥህ ኣለ ነው ያልከኝ
ወቸው ጉድ
እንዲህ ናትና ጣይቱ
እንዲህ ናትና
ሰሙ ጃንሆይ
ሰሙት ወይ
ኣይደረግም፤ ኣይደረግም ኣይደረግም በሉት እንጂ፦

ለሰኣታት በተመስጦ ቁጭ ብለው ነገሩን ሲያሰላስሉ የነበሩት ዳግማዊ ሚኒሊክ፤ እንደ እሳት በሚፋጅ፤ ስል ኣንደበት መናገር ጀመሩ

ኢጣልያዊ ኣፍሪቃ
ኢትይጵያን ባሪያ የማድረግ እጢ
ነጭ እጢ
እባጭ ኣስመራ ላይ በቅሎ
ችንካር ምጽዋ ላይ በቅሎ
ሊያውም በቆዳ ቀላም
ገዢና ተገዢ ህሊና
የበላይነት ኣንጎበር
የቀን ጅብ በውስጡ ኣዝሎ
ወዳጅ ፣መስሎ
በሁለት ጎኑ ተስሎ
ኢትዮጵያን ለባርነት ሴራ
የነጭ ድንጉላ ብዝ ጥዝ ሲል
ፍደል ገልብጦ
ቃላት ደፍጥጦ
ከውል ከስምምነቱ
ከፍቺው ከቃላት ቤቱ
ከቅጂው ከትርጉም ምቱ
ካስተርጉዋሚው ከተርጉዋሚው
ካንቀጽ ገልባጭ ካጭበርባሪው
ከዚህ ሁሉ መንፈስ
የተሻለች ሃገር ነች
ከዚህ ሁሉ ዝብዝብ ትንታግ
ከዚህ ሁሉ ተራ ቡዘት፥ ተራ ጡዘት
ኣንተ ሃገርህን በምታይብት ኣይን እኔም ሃገሬን የማይበት
የፍቅር እውነት ያለኝ ነኝ

የምወዳት ሃገሬ ነች
እንኩዋን ኣንቀጽ ፊደል ቢዛነፍ
ሆኽተ ቅርጹ ኢንኩዋ ቢፋለስ
ኣልደራደርም በክብሬ
ሞግዚት ለማ? ለኔ!? ለሚኒሊክ?!
ሞግዚት ለኢትዮጵያ ነው?
እንዸት ያለ ሙግዝትና
እንዸት ያለ እሹሩሩ
እንኳንስ ጉዲ ፈቻነት
ተው በለው
ነጻ ሁን ብትለኝ እንኩዋ
ካንተ ከሆነ
ነጻነትኽን እንኩዋ ኣልሻም
ሊሬ ምንሽር ስጦታህ ኣይሆንም ዶማ ማረሻ፦

ኢትዮጵያን ነው ያለኝ
ልሞግዝት፤ህ ነው ያለኝ
ኣንቀልባ ልሁንህ ነው ያለኝ
ኣዝዬ እስክጥልህ ነው እኮ
የከክ ፍድፈዳ ደስታ መግሉ ኢስቲፈርጥ ነው

ኣኢትዮጵያን ነው ያለኝ
የልጅነት በረከቴን
የልጅነት ቤቴን
መሰረቴን
የ መስእዋት ቤቴን
መቅደስ ቤቴን
ሸዋ ቢሉ ሸዋነቴን
መሬነቴን
ትግሬ ቢሉ ትግሬንቴን
ጹዋሚነቴን
ጎንደር ቢሉ ጎንደር ቤቴን
መስረቴን
ደቡብ ቢሉ ደቡብ ቤቴን
ጦና ርስቴን
ወሎ ቢሉ ወሎነቴን
ጎጃም ቢሉ ጀግንነቴን
የትኛውን እንድሰጠው ነው የሚማልደኝ

ኣንተ የምትሞትላት ጣልያን እንዳለች ሁሉ
የሚሞቱላት ልጆች ያሉዋት እትዮጵያም ኣለች
በልልኝ
ንገረው፦
ሰውየው ምን ይልክ ነው በለው
ይህንን ነው የሚልክ
ሴትየዋ ጸሃይቱ ነች የቤቴ ብርሃን
ዘውዴ
በልፍኜ ውስጥ የምታፈራ ወይን
ህዝቤ ንብ ነው
ወታደሬ እንደጉንዳንና ኣንበጣ ነው
ባህቴ ዳዊት ነው
በገናዬን በጣቱ
ማህሌቱን በስርቅ ጉሮሮው የወረደና የወጣው ያሬድ ነው
ምልክቴ እንደኣባት ያሳደገኝ ቴዎድሮስ ነው
ስለዚህ መልሴ እምቢ ነው
እምቢ፦
ኣትገዛኝም ኣትሞገዝተኝም
እሹሩሩ
ድግር ና ወገን
የጠመደው እጄ
ላይዳና መንሽ
ያነሳው ክንዴ
ዝሙም ጤፍ ያበራየው በሬዬ
ልጥልጥ በቆሎ እየጋፈረ
ሰርዶ እየነጨ
እየጎደፈረ ያደገው ፈረሴ
መች በጅ ብሎ በለው

ኣንቀልባ መች ኣውቄ
ነብር ሳድን ነው ያደግሁት
ጥቅልል ዘንዶ በካራ ስቀረድ፤ድ ነው ያደኩት
ካናብስት ጋ ስጫወት ነው ያደክሁት
የቤቴ ጌጥ
ጥቁር ኣንበሳ ነው
በልልኝ፦
ስድህ ተደግፌ የተነሳሁት የሸክላ ሌማት ኣይደለም
በልጅ ጥፍሬ ያንበሳ ጎፈሬ ጨብጬ ነው በጉልበቴ የቆምኩት
እና እምቢ ብሎሃል በለው
ሂድ ንገረው፦
ኣምላኬም ከኔ ጋር ነው

ድንግል ከኔ ጋር ነች
የኪዳኑዋ ቃል ከኔ ጋር ነው
ስንዱ ከኔ ጋር ነች
ፍርዱ ለመንገዴ ብርሃን ነው
እየሩሳሌምን የሚጠብቅ እሱ
ኤፍራታንና ዮርዳኖስ ሲፈጥር ኣዳም በኔ ምድር ይመላለስ ዘንድ
ጊዮን የሚባል ርስት
ሰጥቶ ያጸናት ያስራት ሃገር ናት
በሳት ኣትጫወት
ኣይሆንም ካልክ ግን ምን ገዶኝ
ደሞ ኣረም ለማቃጠል
ኩይሳ ለማፍረስ
የዘመን ግቻ ለመንቀል
ና ሞክረኝ ይልሃል በለው;

ንጉስ ሚኒሊክ ይህንን ካሉ ኣንድ ሳምንት ኣለፈ….ኣዋ
እለቱ ቅዳሜ ነበር፤ የገበያ ቀን። ሁለቱ የንጉሱ መልክተኞች ማልደው ተነስተው ስለሚናገሩት ነገር እርስ
በርሳቸው ይነጋገራሉ። ኣዲስ ኣበባ በኣደይ ኣጊጣለች። ከእንጦጦ ተራራ ላይ ሲመለከትዋት በውስጡዋ በረከት
እንደያዘች ታስታውቃለች። በረከቱዋ ግን የጥሬና የጮማ፤ የጠጅና የቁርጥ ብቻም ኣልነበረም ምናልባትም የቁርጥ ቀን
ልጆችንም ጭምር። መልእከተኞቹ ከገበያው እንደደደረሱ ኣንዳችም ጊዜ ሳያጠፉ በገበያው ማህል የንጉሱንና
የእቴጌይቱን መልዕክት ለማስተላለፍ ተብሎ ከተሰራው ማማ ላይ በጥድፊያ ወጡ። ኣተኩሮ ለተመለከታቸው ኣንዳች ጉድ
ይዘው እንደመጡ ፊታቸው ላይ ያለው ቆራጥ ገጽ ይናገራል። ኣረንጉዋዴ ቢጫና ቀይ ቀለም የቀለመ ሸማ የለበሰ ነገር
ተሸክመዋል። እርግጥ ነው እኒህ ሰዎች የንጉሱ ባለሞዋሎች ናቸው እናም ሲጠረጠር የነበረውን ኣንድ መልእክት
ለህዝቡ ሊነግሩት እንደሆነ ግልጽ ነበር። ገበያተኛው፤ ነጋዴው፤ ደብተራው፤ የቆሎ ተማሪው፤ ካህኑ፤ ባልቴቱ፤
መበሊቲቱ፤ ወሰፋው፤ ወሬዛው፤ ኣዛውንቱ፤ ዕማሆዩ፤ ባህቱ፤ስንዴው፤ ገብሱ፤ ኣሞሌ ጨዉ፤ ሙክቱ፤ መሲናው፤
ወሰራው፤ ዳልቻው፤ ዋንኬው፤ጠገራ ብሩ፥ ማሪያ ትሬዛው፤ ባሪያው፤ ምኑ ቅጡ… በገበያው ያልተገኝ፤ ኣለሁ ያላለ
ፍጥረት የለም።ቁሳቁስ፤ ፈንጋይ፤ ተፈንጋይ፤ ጀንደረባ፤ ቁዋንጃ ሽርክት፤ ። ሁሉም ማማው ላይ ከተሰቀሉት ሁለት
ሰዎች ግርጌ ክብ ሰርተው ቁመዋ
በሸማ የተሸፈነውን ነገር ለመክፈት ኣንደኛው ሰው ኣማተበና ቀኝ እጁን ወደ ሸማው ሰደደ፤ ኣብሮት የመጣው ሰው
በክብር ራሱን ዝቅ ኣድርጎ ባይኑ እንዲቀጥል ምልክት ሰጠው። ሸማውን የሚገልጠው ሰው በርጋታና ያርምሞ ቃና ባለው
ዝግታ ነበርና ትእዛዙን የሚፈጽመው፤ ህዝቡ በጉጉት እነዚህ ሁለት ሰዎች ምን ሊገልጡላቸው፤ ሊያሳዩዋቸው፤
እንደሆነ በጉጉት እየጠበቁ ነው። ሸማውን ገልጦ እንደጨረሰ፤ እንደ ጥንታዊያን ግብጣውያን ፓፒረስ ኣይነት ጥቅልል
ብራና ኣወጣ፤ ቀጠለና ከተሸከሙት ትልቅ ቡሃቃ ከሚመስለው ነገር ውስጥ እጁን ጠለቅ ኣድሮግ በመስደድ መለከት
ኣወጣ። ሰውየው መለከቱን ሳያቁዋርጥ ለደቂቃዎች ነፋና የተጠቀለለውን ወረቀት ከፍቶ ከግርጌው ከበውት ቁጭ ላሉት
ሰዎች ማንበብ ጀመረ።በእግዚኣብሄር የምወዳች፤ሁ በስላሴ ጥበብና ፈቃድ የምትወዱኝ ህዝቤ ሆይ፤ መልእክት ከ ነጉስ
ሚኒልክ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ ወ ነገደ ይሁዳ።

ይህቺን የተቀደሰችና የተባረከች ሃገራችንን ከነበረከትዋ፤ ከነክብርዋ፤ ከነ እምነቱዋ እንድትቆይ፤ ድንበራዋን፤
ባህሉዋን፤ ጠብቃ ትኖር ዘነድ ከፈቀዳች፤ሁ እንግዲህ ይህንን ባህሉዋን፤ ያያት የቅድማያት ሃገራች፤ሁን ኢትዮጵያን
ለማፈራረስ የሚፈልግ የውጭ ሃይል በሰሜን በኩል መጥቶዋል።
ህዝቤ ሆይ!
እግዚኣብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት ኣጥፍቶ ሃገር ኣስፋፍቶ ኣኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚኣብሄር ቸርነት
ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ለኔ ሞት ኣላዝንም።ደግሞ እግዚኣብሄር ኣሳፍሮኝ ኣያውቅም።ከንግዲህም
ያሳፍረኛል ብዬ ኣልጠራጠርም።
ኣሁንም ሃገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፤ እግዚኣብሄር የወሰነልንን በር ኣልፎ መጥቶዋልና እኔም
ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም ኣይቼ እስካሁን ዝም ብለው፤ደሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር
ጀመር።ኣሁን ግን በእግዚኣብሄር ረዳትነት ኣገሬን ኣሳልፌ ኣልሰጠውም። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ
ኣይመስለኝም። ኣንተም እስካሁን ኣላስቀየምከኝም።ጉልበት ያለህ በጉልበት፤ህ እርዳኝ ። ጉልበት የሌለህ ለልጅ
ለሚስጥ ለሃይማኖጥ ስትል በህዘን እርዳኝ፤ ወስልተህ የቀረህ ግን ሁዋላ ትጣላኛላህ። ኣልተውህም። ማሪያምን ለዚህ
ኣማላጅ የለኝም።ዘመቻዬ እስከጥቅምት ነውና ፤ የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምቱ እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።
ሁለቱ ሰዎች መልክታቸውን ኣስተላልፈው እንደጨረሱ ብራናውን በጥንቃቄ ጠቅልለው መጀመሪያ መለከቱን ቀጥሎም የብራና
ጥሁፉን በመጥሊቃቸው ውስጥ ካስቀመጡ በሁዋላ ኣረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ቀለም የቀለመውን ሸማ ሸፍነው በርጋታ
ከገበያው መሃል ወጥተው ሄዱ። ህዝቡም የተሸፈነውን የንጉስ ሚኒልክ መልክትና መለከት ይሳለም ነበር። ፍቅር….
የንጉስ ፍቅር፤ የሃገር ፍቅር፤ የመሪ ፍቅር፤ የእውነት ፍቅር፤ የማንንነት ፍቅር። ያ፡የጽድቅ ዘመን። ያ
ኣምላክን የመፍራትና ኣምላክን የሚሰማ ትውልድ የኖረበት ዘመን። የሚኒሊክ ዘመን።

የሚኒሊክ ጦር ….በጣይቱ በኩል በወንድሙዋ በራስ ጉግሳ ወሌ፤ ከሃረር ደግሞ ራስ መኮንን ደጀን በማድረግ
ይዋቀርና፤ የወሎውን ንጉስ ሚኒሊክ፤ የጎጃሙን ንጉስ ተክለሃይማኖት፤ በስተ ሁዋላ ላይ የዩሃንስ ዘውድ ወራሽ
እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ራስ መንገሻን ከትግራይ: ኮዋ ጦናን ከደቡብ ያያዘ ትልቅ ሃገራዊ ጦር ነው።
ጀንደረባው ባልቻ ኣባነብሶ፤ ከእቴጌ ጣይቱ ጋ የተመደበ ኣውራው ጀግናም ነው።
ጉዞ… ጠላትን ለመግጠም ወዳለበት ወደ ትግራይ

ከ ኣንድ ምቶ ሃያ ሺህ በላይ ወጥቶ ኣደር እንዳላቸው የሚነገርላቸው ኣጤ ሚኒሊክ ከወጥቶ ኣደሮቻቸው ጋ
የሚያደርጉት ጉዞ በምን ይመሰል ይሆን?…ታላቁ ሆመር በ ጢሮሳውያንና በኣቴናውያን ዘመን ስለተደረገው ጦርነት፤
ስለ ተርሴሳውያን መርከብና ሰራዊት እልፍነት በገለጸበት ኢልያድ ይሆን፤ የወታደሮቹስ ቀረሮና ሽለላስ፤
የባልቴቶቹስ ደም ግባት፤ የካህናቱስ ዝማሬ ፤ የኣረጋዊያኑ ጸሎት፤ስ

ብቻ ንጉሱ ኣንዳች ኣንዳች ራእይ
ኣንዳች የመለከ መለኮት ትንፋሽ ያሸተቱ ይመስላሉ
ማን ያውቃል፤ ንጉስ ከእግዚያብሄር ነው!
ሰራዊት ባንድነት ይዘምራል
ምታ! ምታ! ምታ! ነጋሪት፤
ክተት! ክተት! ክተት! ሰራዊት
ሰራዊቱ ባንድነት ያዜማል
ከማህለ ማህልየ ሰለሞንም
ከእንደልቤ ዳዊት መዝሙርም
ከያሬድ ማህሌትም ለየት ያለ ቃና ያለው ዜማ

ምታ! ምታ! ምታ! ነጋሪት

ሚኒሊክ ጦርነቱን ካድዋመጀመር የፈለጉበትም ምክንያት ያ ነው። ኣዲግራትን በ ሜጀር ጉሴፒ ጋልያኖ ምርኮኞች
ተከልለው በማለፍ ከጀነራል ባራቴሪ ጋ ሊኖር የሚችለውን ጦርነት በዘዴ ኣለፉት። ኣዋ ኣራተኛው ጉላላት

ሰራዊት ባንድነት ይዘምራል
ምታ፦ ምታ፦ ምታ፦ ነጋሪት፤
ክተት፦ ክተት፦ ክተት፦ ሰራዊት

ኣድዋ
የጥቁር ድል ኣንባ፦

ምታ ምታ ምታ ነጋሪት
ክተት ክተት ክተት ሰራዊት።
ክተት! ክተት! ክተት! ሰራዊት!
የኣኢዛና ሃገር
ኢትዮጵያ
ያምደጽዮን ሃገር
ኢትዮጵያ
የዘራያቆብ ሃገር
ኢትዮያ
የገላውዲዮስ ሃገር
ኢትዮጵያ
የልብነ ድንግል ሃገር
ኢትዮጵያ
የቴዎድሮስ ሃገር ( ከፍተኛ ጭኸት ዕና እልልታ)
እትዮጵያ
ምታ ምታ ምታ ነጋሪት
ክተት ክተት ክተት ሰራዊት
ባብረሃም ዘመንም
ኢትዮጵያ
የማሪያም መቀነት
ኢትዮጵያ
በሙሴ ዘመንም ኢትዮጵያ
የሰው እኩልነት
ኢትዮጵያ
በሶሎሞን ዘመን
ኢትዮጵያ
የ ቃሉ ማደሪያ
ኢትዮጵያ
በቴዎድሮስ ዝመንም ኢትዮጵያ
ለክብር መሰዋት
ኢትዮጵያ
በሚኒሊክ ዘመን ( እልልታ)
ኢትዮጵያ
የነጻነት ደሴት
ምታ ምታ ምታ ነገሪት
ክተት ክተት ክተት ሰራዊ

የሚኒሊክ ሰራዊት ኣላማጠ ድንኩዋኑን በደኮነ ጊዜ፤ የራስ መኮንን ሰራዊት ከ ጀነራል ፒየትሮ ቶኦ፤ሲሊ ጋር
ተናንቁዋል። የራስ መንገሻ ስዩም ሰራዊት በጀነራል ባራቴሪ ሰናፊ ላይ ከደረሰበት ሽንፈት በሁዋላ ከሚኒሊክ ጋ
ተቀላቅሎ የራስ መኮንን ጦር ለማገዝ ተሰልፎዋል። ራስ መኮንን ከኣውሮጳውያን ጋ ባላቸው ቅርበት ምክንያት
በእቴጌይቱ ይጠረጠሩም ስለነበር የኣምባላጌው ጦርነት ጣልያን የማሸንፍ ወይም ያለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ታማኝነትንም
የማሳያ ጦርነት ጭምር ነበር። ጀነራል ፒየትሮ ቶኦ፤ሲሊ የ ራስ መኮንን ጦር፤ ከራስ መነገሻና ከራስ ወሌ ጦር
እጅግ እንደማይበልጥ በደረሰው መረጃ ጦርነቱን እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነበር።
የሆነው ግን ያ ኣይደለም፤ ወደ ኣርባ ሺ የሚጠጋ ሰራዊት የያዘው የራስ መኮንን ጦር የ ጀነራል ፒየትሮ
ቶኦ፤ሲሊን ጦር ኣሽመደመደው።

ኣዋ ኣምባ ኣልጌ ኢትዮጵያዊያኖች ልዩነታቸውን ትተው ጠላትን ባንድነት ድል ኣደረጉ። ኣምባላጌ ላይ የጥቁር ጸሃይ
ወጣች። ኣምባላጌ ላይ ኣፍሪካ ነጻ እንደምት፤ሆን ድል ምስክር ሆነ፦
ኣምባላጌ
የኣፍርቃዊነት መሰረት
የፍቅርም መሰረት
ጮኸ ጠላት
ማሩን ማሩን ፈልገን ኣይደለም ኢዚህ የመጣነው ማሩን
ሰው እንዴት ህሊናውን ለምክንያታዊነት ክፍት ኣያደርገውም። ግራ በተጋባ ህሊና ቀኝ ለመግዛት ማሰብ። ሊያውም
መንገዱ ቀኝ የሆነለትን ንጉስ። እብደት ነው ጥፉ ቢላቸው ነው። እርግማን ነው። ተዋረዱ ቢላቸው ነው። የኣፍሪቃ
ብርሃን ከኛ ይውጣ ሲል ነው።
የነጻነት ብልጭታው ከኣቢሲኒያ ይውጣ ቢል ነው። ኣምላክ ቢወደን ነው። ይሁን ቢባል ነው።

መልክተኛው የሆነውን ሁሉ ለሚኒሊክ ተናገረ። ደስታ ሆነ። ንጉስ ሚኒሊክ ግን ሳቅ ብለው ዝም ኣሉ። የሚሆነውን
ሁሉ ያወቁ ይመስል።

ኣዋ ንጉስ ሚኒሊክ ለማንም ያልተናገሩትን ህልም ኣይተዋል።
ኣሁንም እውነትን ኣሳይሀላው። እንሆ ሶስት ጉልላቶችን እሰራላሁ፤ ኣራተኛው ግን ከሁሉ ይልቅ ይበረታል። በጽኑ
ኣምባ ላይም ኣስቀምጠዋለሁ። ብርሃኑ ከቤቱ ይተርፋል። መሰረቱም ለዘመን የማይናድ ነው። ከስሩ ምንጭን
ኣፈልቃለሁ፤ በተጠሙ ጊዜ ከሱ ይጠጣሉ። የዚያን ግዜም እኔ ያንተ ኣምላክ መሆኔን ትረዳለህ። ዘርህም ባንተ
ክብርን ይወርሳል። በሄዱበት ሁሉ ኣራተኛውን ጉልላት ያነግሳሉ። ግራና ቀኝ በወርቅ በተለበጠ ጥላ የጄ ስራ
የሆነውን ታቦት ይዘህ ኣንተ ኣራተኛ ጉልላቱን ትመሰርታለህ። የጨረሩ ሃይል የሰራዊት፤ህን ኣይን እንዳያጭበረብር
ጊዮርጊስንም ታስከትላለህ፤ ያን ግዜ ፤ የጽዮንን ታቦት ብርሃን እየወነጨፈ፤ ካራተኛው ጉልላት ላይ ያወጣሃል።
የሚያወርድህም የለም። ሰራዊቱም ይታዘዝልህ ዘንድ፤ በድምጸ ልሳንህ ውስጥ፤ የሙሴን በትር ሃይል እሞላዋለሁ።
በቀኝ እጅህ ኣማተበህ በከዘራ ጉልላት፤ህን ታቆም ዘንድ እኔ የእስራኤል ኣምላክ ፈቀድኩኝ። ጉልላት፤ህንም
የምታቆመው ነጭ እጣን ከሚበቅልበት ራማ በቅርብ ርቀት ላይ ካለው ቦታ ላይ ነው።
ካምባላጌው ጦርነት ቀጥሎም ራስ መኮንን ከሜጀር ጉሴፒ ጋልያኖ ጋ ያደረጉት ጦርነት ብዙ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም
በድል ተጠናቀቀ። ንጉሱ ከፈገግታ ያለፈ ነገር ኣላሳዩም። ኣዋ ሶስቱ ጉልላቶች
የራስ መንገሻ ጦር ሰናፌ ላይ ያደረገው ጦርነት፤ የራስ መኮንን ሰራዊት ኣምባላጌና መቀሌ ላይ ያደረገው ጦርነት።
ኣሁን ኣራተኛው ጉልላት። ሚኒሊክ ይህ የሳቸው ጦርነት እንደሆነ በደንብ ያውቃሉ።

ሚኒሊክ ጦርነቱን ካድዋ መጀመር የፈለጉበትም ምክንያት ያ ነው። ኣዲግራትን በ ሜጀር ጉሴፒ ጋልያኖ ምርኮኞች
ተከልለው በማለፍ ከጀነራል ባራቴሪ ጋ ሊኖር የሚችለውን ጦርነት በዘዴ ኣለፉት። ኣዋ ኣራተኛው ጉላላት

ሰራዊት ባንድነት ይዘምራል
ምታ፦ ምታ፦ ምታ፦ ነጋሪት፤
ክተት፦ ክተት፦ ክተት፦ ሰራዊት

ኣድዋ
የጥቁር ድል ኣንባ፦

ምታ ምታ ምታ ነጋሪት
ክተት ክተት ክተት ሰራዊት።

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s