ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ አባቱን የማያውቅ ልጅ ማለት ነው!!


Emperor Haile Silasie Iስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ ሁልጊዜም አብረው የሚነሱ ታላላቅ ሰዎችና ጉዳዮች መኖራቸው አገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስማቸው በበጎ የማይነሳው ንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአህጉረ አፍሪቃ ባበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ ከሀገሬው ይልቅ በውጭ ሀገራት ዜጎች ዘንድ ታሪካቸው በደንብ የሚታወቅና የሚወሳ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን(እኔ የሚያጋጥመኝ) የወሎውን ረሃብ እና የደጃዝማች በላይ ዘለቀን የሞት ፍርድ ብቻ የሰሩ ይመስል ሲብጠለጠሉና ሲወገዙ ነው የሚስተዋለው፡፡
የሆነ ሆኖ የታሪክ ባለሙያም ታሪክ አዋቂም ባለመሆኔ ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያነበብኩትና ከሰማሁት በመነሳት እንደዚህ በአንድ ጎናቸው ብቻ መታየታቸው ባያስደስተኝም . . .ይህንን በዚህ ትቼ . . . አሁንም አዲስ 1879 ቅጽ2 የተሰኘ መፅሃፍ ሳነብ ያገኘሁትንና ‹‹ሻንጣው ብር አምጣ ነገር አታምጣ!›› በሚል ርዕስ ቀረበውን ታሪክ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ይኸው!!

የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅ ከቤተ መንግስታቸው መኖሪያ ቤት የተገኘውን ሻንጣቸውን ለመክፈት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም፡፡ ሻንጣው እጅግ ልዩና ዘመናዊ የሚባል ሲሆን የመክፈቻ ቁልፉ ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ይህ ሸንጣ ብዙ መረጃዎች ስለነበረበት ጥብቅ ጥበቃ ይደረግለት ነበር፡፡ በየቀኑ በተለያየ ዘዴ ሸንጣው የሚከፈትበትን መላ ቢፈለግም ሊገኝ ግን አልቻለም፡፡ የንጉሱ የቅርብ ሰዎች ናቸው የሚባሉ ራሳቸው ሻንጣው እንዴት እንደሚከፈት ሊናገሩ አልደፈሩም፡፡ በጊዜው የነበሩትና ንጉሱን በቅጥጥር ስር ያዋሉት አመራሮች የሻንጣው መከፈት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ከፍተኛ ጥናት ማድረግ ጀመሩ፡ ጥናታቸው ረጅም ጊዜ ወሰደ፡ በመጨረሻም አንድ ፍንጭ ተገኘ፡፡
ንጉሱ ያደረጓት የጣት ቀለበት ትኩረት ተደረገባት፡፡ ወዲያውም ቀለበቷ ከንጉሱ ጣት ላይ እንድትወልቅ ተደረገ፡፡ አስገራሚዋ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀለበት ከነጭ ወርቅ ወይም ከብር የተሰራች ትመስላለች፡፡ በፊት ለፊት ጎበጥ ያለ ቅርጿ በአራት ማዕዘን የተሰራ ሙዳይ መሰል ቅርፅ ያለው ሲሆን በሚያንፀባርቀው የአልማዝ ፈርጧ ላይ የተቀረፀ የቅዱስ ጊዎርጊስ ምስል የሚመስል ንድፍ ተለብጧል፡፡ ቀለበቱ ከተገኘ በኋላ ሻንጣውን መክፈት ግን አልተቻለም፡፡ በቀለበቷ ላይ ሌላ ምርምር ተደረገ፡፡ ከጎን በኩል በብልሃት ቀለበቷን ጫን አሏት፡፡ በረቀቀ ብልሃት የተሰራች ትንሽ መክፈቻ ሰንጢ ተስፈንጥራ ብቅ አለች፡ ብዙዎች ተገረሙ፡፡ ብቅ ያለችውን ሰንጢ መሳይዋን እንደሾለች ከሻንጣው ቀዳዳ ጋር አገናኟት፡ በጥብቅ ይጠበቅ የነበረው የንጉሱ ሻንጣ ተከፈተ፡፡ ሻንጣው ሲከፈት ብዙ ገንዘብ ይገኛል ቢባልም የተገኘው ግን በልዩ ማህደር የተቀመጡ የተለያዩ ሰነዶች ብቻ ነበሩ፡፡ እኒያ ሰነዶች በጥብቅ የሚፈለጉ ነበርና ሰነዶቹ እጅ ወደላይ ተብለው በቅጥጥር ስር ዋሉ፡፡ በጊዜው ትልቅ ደስታ ተፈጠረ፡፡ የሻንጣው መክፈቻ ባይገኝ ኖሮ ሻንጣው በብልሃት ሊቀደድ ተወስኖበት እንደነበር ይነገራል (አዲስ 1879 ቅጽ 2 ገፅ 10)::
***
ትሪካችንን ማወቅ መብታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር መሆን አለበት፡ ምክንያቱም ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ አባቱን የማያውቅ ልጅ ማለት ነው . . . “የጋለሞታ ልጅ!!” እኛ ግን ፈጣሪ መርቆ የወለዳቸው የማያሳፍሩ ጠቢባንና ጀግኖች አባቶች አሉንና አባቶቻችንን እንወቃቸው!!

please enter a message