ፒያሳ ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ (መሀመድ ሰልማን)


መሀመድ ሰልማን ፒያሳ ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ በተሰኘው መጽሃፉ ውስጥ ፒያሳን እንዴት ነበር የገለጻት?
***
ስብሓት “ትኩሳት” ብሎ በጠራው መጽሐፉ ጀርባ ላይ ምን አለ? “ወጣት ሁን” አለ፡፡ ቢመርህ “ሪቮሉሽን” ታስነሳለህ፣ እጅግ ቢመርህ ራስህን ታጠፋለህ…፡፡ ለማንኛውም ወጣት ሁን፡፡ እኔ ግን እልኻለሁ፣ ወጣት መሆኑን ሁን፣ ነገር ግን ራስህን ከማጥፋትህ በፊት ፒያሳ ሂድ፤ ሐሳብህን ልትቀይር ትችላለህና፡፡ ለመሞትም ቢሆን የፒያሳን ያህል መልካም ሰፈር የለም፡፡ ቀባሪ አታጣም፤ በፒያሳ ሰው ባያይህ ማዘጋጃ ያይኻል፡፡ ለመሞትም ለመኖርም ስታስብ ፒያሳ ሂድ፡፡

ፒያሳን ለሞትም ቢሆን የምመርጥልህ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሞት ሞት የሚሸት ስም በድፍን አዲስ አበባ የምታገኘውም ፒያሳ ነው፡፡ “ዶሮ ማነቂያ” ና “እሪ በከንቱ”ን እንደናሙና ውሰድ፡፡ ‹‹ተረት ሰፈር››ም አንተን ተረት ለማድረግ በሚያስችሉ ሕይወቶች የተሞላ መንደር ነው፤ ተረት መሆን ከፈለግህ፡፡ ፒያሳ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ለማጥፋት ጭምር ምርጥ ሰፈር ናት፡፡ ካላመንክ ሙትና ሞክረው፡፡ ነግቶ ሳይመሽ ማዘጋጃ ይቀብርኻል፡፡ ስራ ለማቅለል ከፈለክ ደግሞ እዚያው ማዘጋጃ በር ላይ ጠጋ ብለህ ራስህን መድፋት ትችላለህ፡፡

ፒያሳ ወደ ሕይወትም ልትመልስህ ትችላለች፡፡ “እንዴት?” በለኝ፡፡ ወጣት ነህና ስብሓት በመከረህ መሰረት ራስህን የማጥፋት መብትህን ለመጠቀም ወደ ፒያሳ መጣህ እንበል፡፡ የት ጋር መሞት እንዳለብህ ለመምረጥ በፒያሳ ዞር ዞር ስትል እመነኝ ልብ የምታጠፋ ቆንጆ ታያለህ፡፡ ፀጉሯ የሚዘናፈል፣ ዳሌዋ የሚደንስ፣ ጡቶቿ የሚስቁ… መኖር የምታስመኝ ቆንጆ ልቅም ያለች ውብ 13 ቁጥር አውቶብስ ስትጠብቅ ታያታለህ፡፡ በዚህን ጊዜ ልብህ ይሸፍትና አንተም የተፈጥሮ ሞትህን መጠበቅ እንዳለብህ ትረዳለኽ፡፡ ከዚያች ቅፅበት ጀምሮ የ13 ቁጥር አውቶብስ ቋሚ ደንበኛ ሆነህ ታርፈዋለህ፡፡ አውቶብስና ሞት በራሳቸው ሰዓት እስኪመጡ ትጠብቃለህ። ፒያሳ ወደ ሕይወት መለሰችህ ማለት አይደል?

የፒያሳ ካፌዎች

ፒያሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ካፌዎች ያሉባት ቅመም የሆነች ሰፈር ናት፡፡ አንድ ሺህ አንድ መቶ ቆንጆ ልጃገረዶች ደግሞ በካፌዎቿ ውስጥ ተኮልኩለው ኮካ በ‹‹ስትሮ›› ይጠጣሉ፡፡ ‹‹ስትሮ›› ምን እንደሆነ ካላወቅክ የፒያሳ ልጅ አይደለህም ማለት ነው፡፡ ‹‹ስትሮ›› በቆንጆ ልጅ ከንፈርና በቆንጆ ብርጭቆ መሀል የተሰራ የላስቲክ ድልድይ ነው፡፡
ፒያሳ በካፌ ብዛት “ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ናት፡፡” የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው እንዲህ ያለው ይባላል፡፡ እንደ ፒያሳ በካፌ የተጥለቀለቀ ሰፈር ከየት ይገኛል?! ከአምፒር እስከ ራስ መኮንን ድልድይ ብቻ በግራና በቀኝ የተሰለፉ ከ53 በላይ ካፌዎችን ልቆጥርልህ እችላለሁ፡፡ በእርግጥ ቆንጆ ልጃገረዶችና ወርቅ ቤቶች በመሀል በመሀል እየገቡ ቆጠራዬን አስተጓጉለዉት ይሆናል፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው ከዚህ ቢልቅ እንጂ አያንስም፡፡
የፒያሳ ካፌዎች ልዩ ገፅታ ሁልጊዜ ሙሉ መሆናቸው ነው፡፡

አንዳንድ የፒያሳ ምሁራን ይህንን ጉዳይ ከመንግሥት የትምህርት ፖሊሲ ጋር ሊያይዙት ይሞክራሉ፡፡ እኔ ግን እላለሁ፤ ይህ የፒያሳ ልዩ ከራማ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
በፒያሳ ምርጥ ቡና ጠጥተህ ቀንህን ብሩህ ለማድረግ ካሻህ እነማንኪራ፣ እነ አፍሪካ፣ እነ ቶሞካ አሉልህ…፡፡ ቆንጆ ሻይ ከቆንጆ ልጃገረዶች ጋር ተፋጠህ ፉት ለማለት ካሻህ እነ ናምሩድ፣ እነ ራዜል፣ እነ ኢቪያን፣ እነ ሳሬም፣ እነ ኦስሎ፣ እነ አፕቪው፣ እነ ዲጄስ፣ እነ ሃርድኮር፣ እነ ጉድታይምስ አሉልህ፡፡ በተለይ በቅርቡ የተከፈተው ጉድ ታይምስ እንደ ደብልፌስ ጃኬት አይነት ተፈጥሮ ነበረው፡፡ ቀን ላይ ውብ ካፌ ኾኖ ይቆይና ማታ ላይ በፍጥነት ራሱን ቀይሮ ውብ ባር የመሆን ልዩ ጥበብ ነበረው፡፡ የጨርቆስ ልጆች ያለ ሰፈራቸው መጥተው በቡዳ በሉት መሰለኝ ሰሞኑን ተቃጠለ አሉ፡፡ ነፍስ ይማር!

ፎቅ ላይ ቂብ ብለህ ፒያሳንና ዜጎቿን ቁልቁል እየገረመምካቸው ለመዝናናት ካሻህ አራዳ ላይ የተሰቀሉ መዝናኛዎች አሉልህ፡፡ እነ አራዳ፣ እነ ሲድኒ፣ እነ ትዊንስ፣ እነ ቤስት በፒያሳ ከባህር ጠለል በላይ በምናምን ሺህ ጫማ ከፍታ የሚገኙ ካፌዎች ናቸው፡፡ አለልህ ደግሞ እንደ ዳሎል ተቀብሮ ያለ ካፌ፡፡ ቼንትሮ ይሰኛል፡፡
ልምከርህ! ፍቅረኛህ ፒዛ አማረኝ ካለችህ ፒያሳ ‹‹ፒዛ ኮርነር›› ውሰዳት፤ ከዚያ በኋላ ምን አለ በለኝ ፍቅሯ ካልጨመረ፡፡ ከዚህ ግብዣ በኋላ ካኮረፈችህ ግን ፒዛውን በልተህባታል ማለት ነው፡፡
ፒያሳ የኬክ አገር ናት፡፡ ዕድሜ ጠገቦቹን ….በዚህ አጋጣሚ ስማቸውን ማውሳት ግድ ይላል፡፡ በተለይ የ‹‹ኤንሪኮ›› ኬክ ይምጣብኝ፡፡ እስኪ በሞቴ ከዚህ ቤት ሂድና ኬክ እዘዝ፡፡ ኪኒን ኪኒን የሚያካክሉ ኬኮች ይቀርቡልኻል፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልኾንክ ታኮርፋለህ፡፡ አንተ የለመድከው ድፎ ዳቦ የሚያካክሉ ኬኮችን ነዋ፡፡ እስኪ በሞቴ ቅመሰው፡፡ ከዚያ በአድናቆት ጭንቅላትህን ትወዘውዘዋለህ፡፡ ካልጣመህ ግን በኬክ አላደክም ማለት ነው፡፡ሂድና ሸዋ ዳቦ ተሰለፍ፡፡

ኤንሪኮ ውስጥ ዞር ዞር ብለህ ከጎንህ ያለውን ሰውዬ ገልመጥ ለማድረግ ሞክር፡፡ የሆነ ሰውዬ በትኩረት ኬክ ሲበላ ታየዋለህ፡፡ በእርግጠኝነት ስለሰውየው ብትጠይቅ ከተማዋ ውስጥ ካየኻቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የአንዱ ባለቤት ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ፎቅ ባይኖረው እንኳ ፎቅ የሚሰራ ብር ያለው ለመሆኑ አትጠራጠር፡፡ ይህም ባይኖረው አንድ ቀን የማግኘት ተስፋ ያለው ነው። የኤንሪኮ የውስጥ ገፅታ አለመብለጭለጭ ተራ ቤት እንደሆነ ሊያስገምትህ ይችላል፡፡ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልህ፣ ይህ ቤት የሞጃዎች መናኸሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አትንቀዥቀዥ፡፡

ከኤንሪኮ በኬክ መጋገር ጥበብ ተደንቀህ ስትወጣ ከፊት ለፊትህ የምታገኘው ‹‹እናት ህንፃ››ን ይሆናል፡፡ ይህ ህንጻ በቅርቡ ፒያሳን ከተቀላቀሉ ድንቅ ፎቆች አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ በስነ -ህንፃ ታሪክ በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ከመሆኑም በላይ የሚመስለው የለም እየተባለ ነው፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልኾንክ ይህን ህንፃ ተደግፈህ ፎቶ ብትነሳና ክፍለ ሀገር ላሉ ዘመዶችህ ብትልክላቸው ልጃችን አሜሪካ ገባ ብለው ድግስ እንደሚደግሱ አትጠራጠር፡፡ አዲስ አበባ ውብ ሕንጻ እንደሌለ የሚያስቡ ዲያስፖራዎችም ቢሆኑ እነሱ በማያውቁት አንድ የአውሮፓ ከተማ ያለ ሊመስላቸው ይችላል . . . እያለ ፒያሳን እና በውስጧ የያዘቻቸውን ብርቅየ ነገሮች እንዲሁም በጉዞ ማስታወሻዎቹ በርካታ ከተሞቻችንን ያስጎበኘናል፡ ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ በብዙ ቅጂ የተሸጠና ብዙ አንባቢዎች ዘንድ የተወደደ መጽ ሃፍ ነው እስካሁን ያላነበባችሁ እንድታነቡት ያነበባችሁት ደግሞ ለሌሎች በማዋስ እንድትተባበሩ መልዕክቴ ነው፡፡
– ማንበብ ድንቁርናን ያስወግዳል!! –

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s