ቁራሽ ዳቦ


በ1970ዎቹ አካባቢ ነበር መስፍን ሀርዲመን በኮሎኔል የወታደሮች ቡድን ወደ ፈረንሳይ የተመለሰው፡፡
ወጣቱ መስፍን መሳሪያውን ትከሻው ላይ ጣል አድርጐ፣ ኮፍያውን አይኖቹ ድረስ ደፍቶ እጆቹን በግራ ቀኝ ኪሱ ከቶ ከአንድ መጠጥ ቤት በር ላይ አቀርቅሮ ቆመ፡፡ አይኖቹን መሬት ላይ ሰክቶ የገጠማቸውን እጅግ አሳፋሪ ሽንፈት በማስታወስ በትዝታ ወደኋላ ተጓዘ፡፡
የመጠጥ ቤቱን ግድግዳ ተጠግቶ በጀርባው ያዘለውን ሻንጣ አውርዶ ከከፈተ በኋላ ዳቦ አወጣ፡፡ ዳቦውን አንዴ ገመጥ አድርጐ ማኘክ ሲጀምር መበላሸቱን ጣዕሙ ነገረው፡፡ እስከ ነገ ሌላ ምግብ እንደማያገኝ ያውቃል፡፡ የገመጠውን ዳቦ በምላሱ እያላወሰ በእንግሊዝ ካፌዎች ውስጥ ይመገባቸው የነበሩ ጣፋጭ ኮተሌት፣ በቅቤ የተጠበሰ እንቁላልና ስጋ፣ እጅ የሚያስቆረጥሙ የአትክልት ምግቦችን በህሊናው አስታወሰ፡፡ ትውስታው ዳቦውን መብላት እንዳይችል ምክንያት የሆነበት ይመስል በእጁ የያዘውን ዳቦ ወደ ጭቃ ወርውሮ ያን ያለፈ ጣፋጭ ጊዜ እያስታወሰ ትንሽ እንደተራመደ አንድ ወታደር የወረወረውን ዳቦ በፍቅር አንስቶ ከጠራረገ በኋላ የመጠጥ ቤቱን ግድግዳ ተደግፎ በሚገርም የምግብ ፍላጐት ስሜት ሲበላ ተመለከተ፡፡
ሀርዲመን በሰውየው ድርጊት ሳይገረምና ሳይሸማቀቅ ብሎም ሳይደነግጥ አልቀረም፡፡ ምን አይነት የምግብ ፍላጐት ነው? እንዲህ አይነት አውሬ ተመጋቢም አለ ለካ? ሲል በውስጡ ተገረመ፡፡
ሰውየው ቀጭንና ረዘም ያለ ሲሆን ትከሻው ሰፊ ነው፡፡ ፊቱም በጺም ተወርሯል፡፡ የገረጣ ፊቱን ተመልክቶ አመድ የመሰለ ጺሙን ላስተዋለ ሰው፣ ሰውየው ለረጅም ጊዜ በድህነት የኖረ ስለመሆኑ መገመት አይገደውም፡፡
ሀርዲመን ወደ ወታደሩ ቀረብ አለና “በጣም ርቦህ ነበር?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ያው እንደምታየው መሆኑ ነው ነገሩ” የመጨረሻ ጉርሻውን እየዋጠ መለሰ ወታደሩ፡፡
“እንግዲያውስ ይቅርታ አድርግልኝ! ምግቡን የምትፈልገው መሆኑን ባውቅ ኖሮ አልጥለውም ነበር”
“ኧረ ምንም ችግር የለውም፡፡ የሚበላ ተገኝቶ ደግሞ እንዲህ ሊባል ነው?” ሲል መለሰ ወታደሩ፡፡
“ድርጊቴ ፀፅቶኛል፡፡ ምግቡን መጣል አልነበረብኝም” አለ ሀርዲመን
“ኧረ ግድ የለዎትም፡፡ እርስዎ ይህን አላሰቡት ይሆናል” አለ ወታደሩ
“እንግዲያውስ አንዲት በትንሽዬ ጠርሙስ ያለች ግማሽ ብራንዲ አለችኝና አብረን ብንጐነጫት” አለ ሀርዲመን
ዳቦውን በልቶ የጨረሰው ወታደር በሀርዲመን ሃሳብ ተስማምቶ ብራንዲዋን አብረው ተጐነጩ፡፡
“ታዲያ እርስዎን ማን ልበል?” ወታደሩ መስፍን ሀርዲመንን ጠየቀው፡፡
ሀርዲመን ማዕረጉን ሳይጨምር ስሙን ብቻ ነገረውና፤
“ያንተስ?” አለው፡፡
“ዥን ቪክቶር እባላለሁ፡፡ በቻቲሎን አካባቢ ስለቆሰልኩኝ እዚህ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ እርዳታ እየተደረገልኝ ነው፡፡ የጭረት ያክል ነበር የቆሰልኩት፡፡ በሆስፒታሉ የከባድ ቁስለኛ ልዩ ማቆያ ክፍል የፈረስ ሾርባ እየጠጣሁ ጥሩ ጊዜ ነበር የሳለፍኩት፡፡ ይሁንና ዋና አዛዡ የማሰናበቻ ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ ያኔውኑ ነበር ወደነበርኩበት ረሀብ ዳግመኛ መመለሴን የተገነዘብኩት፡፡ ይገርምሃል ጓዴ እንደምታየኝ እድሜ ዘመኔን ሙሉ ስራብ ነው የኖርኩት፡፡ እመነኝ ጓዴ እድሜዬን ሙሉ ስራብ!”
የወታደሩ ስሜት የተቀላቀለበት አነጋገር የእንግሊዝ ካፌዎች ለናፈቁትና ምቾትን ለሚሻው ሀርዲመን አስገራሚ ነበር፡፡ ሀርዲመን ወታደሩን ድንጋጤ በሚነበብበትና በጥልቅ አግራሞት ሲመለከተውና ወታደሩም ሀዘንን በሚያንፀባርቅ ገጽታ ፈገግ ሲል የተራቡና የተኩላ የሚመስሉ ነጫጭ ጥርሶቹ ከገረጣውና ከሰልካካ ፊቱ ጋር ይታያሉ፡፡ ወታደሩ በራስ መተማመን በተሞላበት አንደበት እንዲህ አለ፡-
“ና ጓዴ እግራችንን ለማፍታታት ያህል ትንሽ ዞር ዞር እንበል እስኪ፡፡ እኔ ተጥሎ የተገኘሁ ልጅ ነኝ፡፡ ለዚያ ነው ዥን ቪክቶር ብቻ ተብዬ የምጠራው፡፡ ምንአልባትም ሰምተኸው የማታውቀውን ታሪኬን ላጫውትህ” አለ ወታደሩ – በቅንጦትና በደስታ ላደገው ሀርዲመን፡፡
“አሳዳጊዬ በሳንባ በሽታ ከመሞቷ በፊት በዚያ አዳሪ ት/ቤት ውስጥ ከህጻናቱ ጋር ከመጫወት ይልቅ ከእሷ ጋር መሆንን እመርጥ ነበር፡፡ አቅፋ ፀጉሬን እያሻሸች ታስተኛኝ ስለነበር ከልቤ ነበር የምወዳት፡፡ እሷም ከሁሉም ህጻናት አብልጣ ትወደኝ ነበር፡፡ በኋላ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ በርካታ ማየት የተሳናቸው ልጆችን ወደ ት/ቤቱ ሲያመጣ የምንበላው ዳቦ እየቀጨጨ ሄዶ ጭራሽ ወረቀት የመሰለ ዳቦ መብላት ጀመርን፡፡ አስተዳዳሪውና ባለቤቱ ከሞቱ በኋላ ደግሞ ረሀብ መጣ፡፡ ከእኔ ጋር ይመገቡ የነበሩት ሁለቱ ዓይነ ስውራን ልጆችም በአመጋገባችን ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ያን እንደ ወረቀት የሳሳ ዳቦ አንዴ ከሰጡን በኋላ ቀሪውን ቆልፈውበት ይሄዳሉ፡፡ ያኔ በጣም ነበር የሚርበኝ፡፡ እና ይሄ ሁኔታ የኔ ስህተት ነው? አይመስለኝም፡፡ እንደዚያ እየራበኝ ለሶስት አመት ያህል በእንጨት ስራ አገልግያለሁ፡፡ ሶስት አመት ሙሉ አየህ! የእንጨት ስራ ስልጠናው ግን የአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ ቅድም የጣልከውን ዳቦ አንስቼ ስበላ ተገርመህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን ከዚያ አስር እጥፍ የባሰና የደረቀ ዳቦ ሳገኝ በውሃ ወይም በምራቄ እያራስኩኝ እንክት አድርጌ ነው የምበላው፡፡ ይኸውልህ ጓዴ፤ አንዳንዴ መልዕክት ለማድረስ በምላክበት ጊዜ እግረ መንገዴን ንፋስ የጣለውን የዛፍ ፍሬና ህጻናት ወደ ት/ቤት ሲሄዱ የጣሉትን የምግብ ትራፊ እየሰበሰብኩ ረሀቤን ለማስታገስ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ ከዚህ አስከፊ ረሀብ ለመላቀቅ ስል ድንጋይ ጠራቢነት፣ ሱቅ ጠባቂነት፣ ጽዳት ከዚያም ወዛደርነት ብሰራም ራሴን በበቂ ሁኔታ መመገብ አልቻልኩም ነበር፡፡ ዳቦ ጋጋሪነት መስራት ስጀምር ለትንሽ ጊዜ ቢሆንም ከረሀብ ርቄ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እየኖርኩ ሳለ አቅፋ ፀጉሬን እያሻሸች፣ ትሁትና ታማኝ እንድሆን አሳዳጊዬ ትመክረኝ የነበረውን ሁሌም አልዘነጋውም፡፡”
ለአመጋገቡ እንደሚጠነቀቀው ሁሉ ለአለባበሱም የሚጨነቀው ሀርዲመን፣ የዚህን ተራ ወታደር አሳዛኝ ታሪክ በእርጋታ አዳምጦ ሲያበቃ በከባድ ሀዘን ተዋጠ፡፡ አይኖቹ በእንባ ተሞሉም፡፡ ሀርዲመን ወታደሩን በሀዘኔታ ካስተዋለው በኋላ፤
“ካለኝ የምግብ ፍላጐት አንጻር የእኔ የምግብ ድርሻ በእጥፍ የሚበልጥ ስለሆነ ከአሁን በኋላ ስለ ምግብ አታስብ፡፡ ልክ እንደ መልካም ጓደኞች ሆነን ከቁርስ እስከ እራት ድረስ ሁሌም ከድርሻዬ አካፍልሃለሁ” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ዥን ቪክቶር እጅግ ተደሰተ፡፡ ሌሊቱን ለማሳለፍ ከወጥ ቤት የወረደ ገጽታ ወዳላትና በሳር ወደተሰራችው የዥን ቪክቶር ማደሪያ አብረው ሄዱ፡፡ ዥን ቪክቶር ረሀብ እንቅልፍ ስለከለከለው እኩለ ሌሊት ላይ ተነሳ፡፡ ወርቃማና የሴት የመሰለ ፀጉሩ በጨረቃዋ ብርሃን የሚያበራው ሀርመዲን ግን እዚያው አልጋው ላይ ተኝቶ ይታያል፡፡ ዥን ቪክቶር የተኛውን ሀርዲመንን እየተመለከተ ስለ ሩህሩህነቱና ደግነቱ አሰበ፡፡
በዚያ ድቅድቅ እኩለ ሌሊት የወታደሮቹ አዛዥ አንድ በር እያንኳኳና የአንድን ተረኛ የጥበቃ ሰራተኛ ስም ሲጣራ ተሰማ፡፡ አዛዡ ከሚጠራቸው ስሞች መካከል የሀርዲመን ስም ይገኝበታል፡፡ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ያለው ሀርዲመን ግን ጥሪውን አልሰማም፡፡
“ይቅርታ አዛዥ! ሀርዲመን ከባድ እንቅልፍ ውስጥ ነው፡፡ ፈቃድዎ ከሆነ እሱን ተክቼ የጥበቃ ስራውን እንዳከናውን ቢፈቅዱልኝ” በማለት ዥን ቪክቶር ለአዛዡ ጥያቄ አቀረበ፡፡
“ትችላለህ” አለ አዛዡ
ዥን ቪክቶር የሀርዲመንን ቦታ ተክቶ ከአራት ተረኛ ወታደሮች ጋር በመሆን ወደ ጥበቃ ስራው ተሰማራ፡፡ ይህ ከሆነ ከግማሽ ሰዓት በኋላ በአካባቢው የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡ በተኩሱ ድምጽ ከእንቅልፉ የነቃው ሀርዲመን፤
“ስንት ሰዓት ነው? ኧረ እባካችሁ ተረኞች ነን፡፡” በማለት ከሳር ቤቷ አጠገብ ባሉ ቤቶች ውስጥ የተኙትን ጠየቀ፡፡
“ዥን ቪክቶር አንተን ተክቶ ሊሰራ ሄዷል” በማለት አንድ ወታደር መለሰለት፡፡
ወዲያውም ለጥበቃ ከወጡት ወታደሮች መካከል አንዱ ወደ ሳር ቤቷ እየሮጠ በመምጣት ፐርሺያኖቹ ጥቃት እንዳደረሱ ገለፀ፡፡
“ጓዶቹስ?” ሀርዲመን ለወታደሩ ጥያቄ አቀረበ፡፡
“ከዚያ ምስኪን ዥን ቪክቶር በስተቀር ሁሉም አምልጠዋል” መለሰ ወታደሩ
“ዥን ቪክቶር!” አለ ሀርዲመን በከባድ ድንጋጤ ተውጦ
“አዎ! ምስኪኑ ዥን ቪክቶር ጭንቅላቱን በጥይት ተመቶ አንዲት ቃል እንኳ ሳይተነፍስ ነው የወደቀው” ሲል ወታደሩ ሀዘን በተሞላበት ቅላጼ መለሰ፡፡ ሀርዲመን በአንድ የክረምት ወቅት አመሻሽ ላይ ሳሉሰን ከሚባል መስፍን ጋር እየተዟዟረ ሳለ ቁራሽ ዳቦ ወድቆ አየ፡፡ ዳቦው ጭቃ የነካውም ነበር፡፡ ሀርመዲን ዳቦውን አንስቶ በትከሻው አንጠልጥሎ በያዘው ቦርሳ ውስጥ ከተተው፡፡ ይህን የሀርዲመንን ድርጊት የተመለከተው መስፍን ሳሉሰን፤
“አንተ አብደሃል! ጭቃ ላይ የወደቀ ዳቦ አንስተህ ልትበላ ነው እንዴ?” በማለት እየሳቀ ጠየቀው፡፡
“ይህ በጭቃ የተለወሰ ቁራሽ ዳቦ ቅንጣት ሳይሳሳ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠልኝ የወታደሩ ዥን ቪክቶር ማስታወሻ ነው፡፡ በክብርም አኖረዋለሁ፡፡ አትሳቅ ከምሬ ነው” በማለት ለመስፍኑ የአግራሞት ጥያቄ ሀርዲመን መልስ ሰጠ፡፡
Source:-Addis Admass

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s