ማህሌት


የሆነ ያልገባው ነገር አለ፡፡ ስለ ህይወቱ? … ስለ እናቱ? በተለይ ስለ አባቱ? … በጥቂቱ ደግሞ ስለ ትምህርቱ፡፡ እንደ ድሮው አይደለም እሱነቱ፡፡ “ኤሊየን” ስለመሆኑ እንደ ድሮው ከዚህ ስምንት አመት በፊት አያምንም፡፡ እንኳንስ… አፍ አውጥቶ መናገር፡፡
የአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርት እንደሚወራለት ከባድ አይደለም፡፡ ትንሽ አስተማሪዎቹ የሚሉትን መስማት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ደብተር ይዞ አያውቅም፡፡ አስተማሪ ተብዬዎቹ የሚያወሩትን ሰምቶ ፈተና በተባለው ወረቀት ላይ ሲደግምላቸው ይደሰታሉ፡፡ ሲደሰቱ “አንደኛ” ወጥተሃል ይሉታል፡፡
ዘጠነኛ ክፍል እያለ እንደዚያ አስደስቷቸው ነበር፡፡ አመቱን ሙሉ እነሱ የሚሉትን እንደ “ፓሮት” ደገመላቸው፡፡ አመቱን ሙሉ፡- ማለትም ሁለት ሴሚስተር ያህል “አንደኛ” ነህ አሉት፡፡ “አንደኛ” እና “አንተ ነህ” አሉት፡፡ ስሙ እና እውነተኛ ማንነቱ የጠፋው ሲመስለው፤ አስረኛ ክፍል አስተማሪዎቹ የሚሉትን መድገም አቆመ፡፡ “አንተ አይደለህም” ቢሉትም አልጣሉትም፡፡ “ወደቀ” ብለው አሾፉበት እንጂ ሰርተፍኬቱ ላይ “ወደቀ” ብለው አልፃፉበትም፡፡
ዘጠነኛ ክፍለ ፊት ወንበር መጀመሪያ መደዳ ነበር የሚቀመጠው፡፡ አስረኛ ክፍል መጨረሻ መደዳ ተቀምጦ “ሮበርት ሉድለምን” እያነበበ፣ በደረጃ መጨረሻ እየወጣ አመቱን ጨረሰ፡፡ መጨረሻ መደዳ የሚቀመጡት ፊት የሚቀመጡትን እንደ “ባንዳ” እንደሚቆጥሯቸው የተረዳው ከእነሱ መሀል ሲቀመጥ ነበር፡፡ ፊት ወንበር የሚቀመጡት ኋላ ያሉትን ምን ብለው እንደሚጠሯቸው ግን በመሀላቸው ሳለ አልነገራቸውም፡፡
ከኋለኛው መደዳ ረድፈኞች ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ያለፉት የተወሰኑት ናቸው፡፡ ከተወሰኑት መሀል ማህሌት አንዷ ናት፡፡ በመጀመሪያው ሴሚስተር ከሮበርት ሉድለም መፅሐፍ ማህሌትን ወደ ማጥናት አደገ፡፡ የእሷን ትኩረት ለመሳብ ሲል መሆን አለበት… ኋላ መደዳ ተቀምጦ ፊት ተቀማጮቹ የሚታሙበትን ነገር ማድረግ ጀመረ፡፡ ማጥናት፤ በአጭር ቋንቋ አስተማሪው የሚያዘውን ሁሉ ማድረግ፡፡ የሚደግመውን መድገም፡፡ ተመልሶ ፓሮት ሆነ፡፡
አስተማሪዎች ይገርሙታል፡፡ እነሱ ያሉትን ሁሉ አንድ ሳያስቀር ኮፒ አድርጎ የሚገለብጠውን ልጅ የፈተና ወረቀት ሲያርሙ፣ የእስክሪብቷቸው የቀይ ቀለም ጭነት ራሱ ይለሰልሳል፡፡ የሚወዱትን ልጃቸውን ጭንቅላት የሚያሹ ነው የሚመስሉት፡፡ “መቶ ከመቶ”፣ “ስልሳ ከስልሳ”… “ኤክሰለንት”… በ“Very Good” እና በ“Excellent” መትረየስ ወረዱበት፡፡ “አንተ ነህ” አሉት፡፡
ከማህሌት ጋር ለመተዋወቅ ቀላል ነበር፡፡ ያው ምክኒያት አያስፈልግም፡፡ “እቺን ነገር አሳየኝ!” “ያቺን ነገር አሳየኝ?”…
ስሙ አስተማሪዎቹ እንደሚጠሩት “አንተ ነህ” ሳይሆን…፣ ሚልኪ እንደሆነ አስረግጦ ነገራት፡፡ የተለያየ ቦታ፣ የተለያዩ ሰዎች የሚያወጡለት ስም እንዳለ ግን ደበቃት፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ በነበረበት ሰፈር “Ace” እያሉ እንደሚጠሩት፣ ጥሪውን ግን ሰፈር ሲቀይር እንደተለወጠ መናገር ዋጋ የለውም፡፡ አባቱ የሚጠራው ስምም አለ፡፡ መውደድ ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ አይን ስለ አይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፡፡
አሁን ከማህሌት ጋር ሚልኪ በሚለው ስሙ ነው መቀራረብ የፈለገው፡፡ መታወቂያው ላይም ስም አለው፡፡ በሱም ስም ሰዎች ይጠሩታል፡፡ ሁሉንም ጥሪ አቤት ብሎ ይቀበላል፡፡ ከነብሱ አንደበት ራሱን የሚመራበትን ስም ግን በአፉ ለራሱ እንኳን ቢሆን ጮክ ብሎ አይደግምም፡፡ ጉልበቱ የት እንደሚገኝ እንደ መግለፅ ይመስለዋል፡፡ ሳምሶን ጉልበቱን ፀጉሩ ላይ አስቀምጦ፣ ፀጉሩ እንደ በግ ሲሸለት፣ በግ እንደመሰለው …. እሱም ስሙን ምላሱ ላይ አስቀምጦት፣ ምላስ ያላቸው ሁሉ በእሱ ጉልበት እጣ ፈንታቸውን እንዲሸከሙ አይፈቀድላቸውም፡፡
ከማህሌት ጋር ተግባባ፡፡ ከማህሌት ጋር ሲቀራረብ፣ ከራሱም ማንነት ጋር ሆነ፡፡ አስተማሪዎች ማን እንደሆነ እየደጋገሙ ከሚደሰኩሩለት ራቅ ያለ ሶስተኛ ማዕዘን ላይ የተቀመረ መሆኑ ለራሱ ይሰማዋል፡፡ ቢሰማውም ይሄንን ሶስተኛ ማንነቱን ወደደው፡፡ ከወትሮው የሦስት መአዘን አቋሙ ጋር የሚስማማ ነገር ስላለው፡፡
በፊት እናቱ ከአባቱ ጋር አንድ ላይ በሚኖሩበት ጊዜ፣ እሱ የእናቱንም ሆነ አባቱን ወይንም አባቱ እሱን እንደሚያየው ወይንም እናቱ እሱን በምታየው አንፃር ራሱን ተመልክቶ አያውቅም፡፡ ሁሌም ሶስት መአዘን ይይዛል፡፡
በዚያ የልጅነት ዘመን ጎረቤቱ ያሉት እዮብ እና ናትናኤል ምርጥ ጓደኞቹ ነበሩ፡፡ ሁለቱም እሱን እንደሚያዩት .. የራሱን እይታ አመቻችቶ አያውቅም፡፡ የእዮብ እና የናትናኤል አባት ኢንጂነሩ በጣም ያደንቁት ነበር፡፡ “Ace” የሚለውን ለእነሱ እይታ የሚሆን ስም አውጥተው እንዲፀድቅ አድርገዋል፡፡ እነሱ እሱን እንደሚያዩት እንጂ እሱ እነሱን መልሶ እንደሚያያቸው… በማየት እና በመታየት መሀል ትልቅ ክፍተት እንዳለ አይገነዘቡትም ነበር፡፡ እነሱ እሱን ለመካብ የሚሰጡትን ስም እንጂ እሱ እነሱን ለማድነቅ ያወጣላቸውን ስያሜ አያውቁትም፡፡ እነሱ በሚያዩበት አለም ሁሉንም ብያኔ ለመስጠት የሚያስችል ንግስና እንዳላቸው፣ እሱም በራሱ ዓለም ውስጥ ለሚታዩት ነገሮች ብያኔ የመስጫ ልዕልና መጎናፀፉ ይረሳቸዋል፡፡
ከማህሌት ጋር ሲሆን አፍቃሪ እና ተፈቃሪ … ከመምህሮቹ ጋር ሲሆን ተማሪና አስተማሪ … ከእናቱ ጋር ሲሆን በአንድ ጊዜ ልጅ እና ወላጅ መሆን እንደሚችል ማንም አይገነዘብለትም፡፡ አብዛኛው ሰው የሚታየው አሀዳዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የራሱ መንገድ፡፡ የራሱ ፍላጎት መንገድ፡፡ ኤስ ግን ሶስት መንገድ በአንድ ጊዜ ይታየዋል፡፡
በማህሌት ላይ የሚያየው መንገድ የዚህን ባህርይ የተላበሰ ነው፡፡ አንደኛው መንገድ እሱ እሷን ለማፍቀር፣ ጓደኛ ለመሆን፣ አብሮ ለመሰንበት የሚያሳየው ፍላጎት የሱ ፈቃድ ነው፡፡ ሁለተኛው ማህሌት ከሱ የምትፈልገው፣ እንዲሆንላት የምትመኘው፣ የሷ እምነት፣ እሱን በመቆጣጠር የሚፈጠረው መንገድ ነው፡፡ ሶስተኛው ከሁሉም ውጭ የሆነው ነው፡፡ ሁሉንም መሆን እና አለመሆን በአንድ ላይ የሚችለው መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ እንደ እውነተኛው ስሙ እውነተኛው “ህቡዕ” ምንነቱ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡
የማህሌት መንገድ እና የእሱ መንገድ፤ ከዚያ ሶስተኛው መንገድ፡፡ ማህሌትን እያስጠናት እሱ ደግሞ እሷን ያጠናት ጀመር፡፡ እሷም እያጠናች እንደምታጠናው ያውቃል፡፡ ሁለቱንም ጥናቶች ከውጭ ሆኖ ሶስተኛው መአዘኑ ላይ ይቆምና ይከታተላል፡፡ ሲከታተል አስተማሪዎቹን፣ ተማሪዎቹን እናቱን፣ ህይወቱን አንድ ላይ ጠቅልሎ ነው፡፡
የማህሌትን ውጤት ዝቅ ካለበት ከፍ ሲል እያየ፣ የራሱን ከፍ ካለበት እንዲወርድ ፈቀደ፡፡ የአስተማሪዎቹ እይታ ስለሱ ወይንም ስለሷ … ስለ እሷና እሱ መርገብገቡ ከማይርገበገበው መአቀፋዊ ምዘናው ላይ ሆኖ እንደገና ይለካል፡፡
ከአስተማሪዎቹ መሀል አንደኛው… ግጭት ለመፍጠር ከመንጋው መምህርነት ወጥቶ ወደነሱ ግንኙነት ተጠጋ፡፡ አስተማሪው የባይሎጂ ትምህርት የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለትምህርቱ ሰውየውም የተሰጠ መሆኑ በስፋት ይነገርለታል፡፡ የሚነገርለትን ያለ ይሉኝታ ከመናገርም ሰውየው ራሱ አይቦዝንም፡፡ ለትምህርቱ ባሳየው ተነሳሽነት ብዙ ሽልማቶችን ሰብስቧል፡፡ ባዮሎጂ ህይወትን የሚያጠና በመሆኑ፣ አስተማሪው ከህይወት አይነቶች መርጦ ቆንጆ ሴቶችን መመርመር ይወዳል፡፡ የወደደውን ይመረምራል፡፡ ማህሌት የቆንጆ ሴቶችን መስፈርት የምታሟላ “እስፒስመን” ናት፡፡
በተሰጠው ክፍለ ጊዜ በጥቁሩ ሰሌዳ ላይ የሚፅፈውን ፅፎ ወይንም የሚያብራራውን አብራርቶ … ትንፋሽ ለመውሰድ የሚያመራው ወደ ማህሌት አቅጣጫ ነው፡፡ ደብተሯን ያገላብጣል፡፡ ደብተሯን በእጁ፣ መልኳንና ተክለ ሰውነቷን በአይኑ፡፡ ስህተት ሊያገኝባት ይታትራል፡፡ የሚፈልገውን ባያገኝም በአለባበሷ ላይ እንደ አባት ይሆንና ተግሳፅ ይሰጣል፡፡ እንደ አባት የጀመረው ምክር እንደ አጎት ይመስልና እንደ መሸታ ቤት ተስተናጋጅ ሆኖ ይጨርሳል፡፡ በተለያየ ጊዜ ቢሮ ጠርቷት ከባዮሎጂ ጋር በጣም ስለሚገናኙ የፆታዊ ባህሪዎች በጥያቄ መልክ አቅርቦለታል፡፡ አቅርቦልኛል ብላዋለች ኤስን፡፡
ሰው ሰማም አልሰማም፣ ሰውየው ለልጅቱ አንዳች ጥላቻ አለው፡፡ ተንጠራርተው የሚደርሱበትን ነገር እንደሚጠሉ ሰዎች ይመስላል… ማህሌትን ሲያያት የሚያሳየው መንገሽገሽ፡፡
“ንፍጥ” የሚል ስድብ ወደሷ አቅጣጫ ይሰነዘራል፡፡ የባዮሎጂ ተራ አስከባሪ በመሆኑ፣ ለትምህርቱ አምልኮት ያላቸው የፈተናውን ወንዝ ለመሻገር ይስቁለታል፡፡ ኤስ በዚህ ሁሉ ውስጥ የተመልካች ስፍራውን ይዞ ይታዘባል፡፡ መታዘብ ባበዛ ቁጥር ለምን ወደ አንዳች አቅጣጫ እያደገ መሆኑ እንደሚሰማው ለራሱም ማስረዳት አይችልም፡፡
ከእለታት በአንዱ ቀን በሰሌዳው ላይ የተለቀለቀውን ጽሑፍ ተማሪዎቹ እንደ እርግብ በእስክሪብቶው መንቁራቸው እየለቀሙ ሳሉ… እህሉን ያፈሰሰላቸው መምህር ወደ ማህሌት መቀመጫ ሄዶ፣ እለታዊ ጉንተላውን አከናወነ፡፡ በመቀጠል ነጭ ጋውኑን አንዘርፍፎ ከእሷ አንድ ረድፍ በቀደመው ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ አስተማሪው የራሱን ጽሑፍ በተማሪ አይን ከኋላ ሆኖ መገምገም ጀመረ፡፡
ኤስ እንደ ሌሎቹ የተፃፈለትን ሁሉ አይለቅምም፡፡ ከሮበርት ሉድለም ወደ ጄምስ ካለቬል ድርሰት አድጓል፡፡ “ሾ ጋንን” እያነበበ ነው፡፡ አስተማሪው ሲያነብ ያየዋል ግን አይተናኮለውም፡፡ “አንተ ነህ” የሚለው ማዕረጉ፣ የሌላው ተማሪ ግዴታ እንዳይመለከተው መንገድ ሰጥቶታል፡፡ ግን ይህ የባዮሎጂ መምህር ስህተት ቢያገኝበት ሊጥለው እንደሚፈልግም ያውቃል፡፡ ከመከባበር ይሁን… ከመገማገም የመጣ መፈራራት በመሃላቸው ሰፍኗል፡፡ ኤስ ከማህሌት ጐን መቀመጡ የአስተማሪው የቀድሞ ፍቅር ወደ “ቆይ ጠብቅ” ሲቀየርበት ይታወቀዋል፡፡
ኤስ እና ማህሌት ከተቀመጡበት መደዳ ፊለፊት የተዘረፈጠው የባዮሎጂ አዋቂ በፈዘዘበት አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ ኤስ ልጅ በነበረበት ወቅት አንድ ነገር ከመከሰቱ ጥቂት ቅጽበት ቀደም ብሎ የሚከሰተውን ነገር ያውቀው ነበር፡፡ ለምሳሌ አስተማሪ በሰሌዳው ላይ የሚያሰፍረውን ጽሑፍ ጥቂት ቀደም ብሎ ሰፍሮ ይታየው ነበር፡፡ ግን ይህ ችሎታውን ሳያዳብረው፣ ከሰው ተወራርዶ ሳይረታበት፣ በራሱ ውስጥ እንደያዘው እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ቀስ በቀስ ችሎታው ጠፋበት፡፡
ጠፍቶበት ቆይቶ ልክ በዛች ቅፅበት አስተማሪው ከፊለፊቱ የእነሱን ዴክስ ተደግፎ በተቀመጠበት፣ ያ የተዘነጋ ችሎታው ድንገት ተከሰተለት፡፡ ማህሌት ቀጥላ የምታከናውነው ተግባር ታየው፡፡ ታየው፤ ግን ነገሩን ከመከሰት ለማቆም ምንም እርምጃ አልወሰደም፡፡ ሶስተኛው መአዘን ላይ ያቆመው ዋነኛው ሚዛን፣ የተከሰተውን ተግባር መግታት ይችል የነበረውን የእሱን እጅ ከውስጥ ያዘበት፡፡ Kay sera sera
ማህሌት ከሰሌዳው ላይ መገልበጧን ድንገት አቆመች፡፡ በፈጣን ትልልቅ ፊደል ለአስተማሪው እንዳይሰማው አድርጋ፣ ከጀርባ በነጩ ጋውን ላይ “የሰው ንፍጥ” ብላ ፃፈች፡፡
* * *
የትምህርት ጊዜ አለቀ፡፡ ሰውየውም የእውቀት ማቀበያ መሳሪያዎቹን (ቾክ እና ዳስተር) አንከብክቦ ወደሚቀጥለው ክፍሉ አመራ፡፡
ተቀያሪው አስተማሪ አንድ እግሩ አጠር የሚል፣ ጮክ ባለ ድምጽ የአማርኛን ሰዋሰው የሚያስጨብጥ ሰው ነበር፡፡ አስጨብጦ ሲጨርስ ረዘም ካለው እግሩ አጠር ወዳለው ወርዶ እረፍት ይወስዳል፡፡ መናገር ሊጀምር ሲል እንደገና ከአጭሩ ወደ ረጅሙ ይወጣል፡፡ ሁሉም አስተማሪዎች ቅጽል ስም አላቸው፡፡ ቅጽል ስሞች በአብዛኛው የሚወጡት ፊት መደዳ ከሚቀመጡት ተማሪዎች አይደለም፡፡ ጭቆና ከላይ ወደ ታች እንደሚበረታው፣ ቅጽል ስም ደግሞ ከታች ወደ ላይ የሚስፈነጥር ፍላፃ ነው፡፡ ፍላፃው ግን በተወረወረበት አካል ጆሮ ውስጥ ብዙውን ጊዜ አይገባም፡፡ እኩል እግር የሌለውን አስተማሪ “ሲትሮይን” በሚል ስም ነው ኋለኞቹ የሚጠሩት፡፡
ሲትሮይን፤ ትምህርቱን አስተላልፎ ለማብቃት ሁለት የቁመት ማጠር እና የማስረዘም ያህል ጊዜ ሲቀሩት፣ የክፍሉ በር በእርግጫ በመሰለ ሀይል ተመትቶ ተከፈተ፡፡ የባዮሎጂው መምህር የሹራብ ሰደርያ እና ጉርድ ሸሚዝ እንጂ ነጩን ጋውን አልለበሰም፡፡
ነጩ ጋውን እንደ ኤግዚቢት በዩኒት ሊደሩ እጅ ተይዟል፡፡ ዩኒት ሊደሩ በጣም ረጅምና በጣም ጥቁር አስፈሪ ሰው ነው፡፡ እውቀት ባያንሰውም ችግርን በዱላ በማስከበር ተፈሪነትን ያተረፈ ሰው ነው፡፡ ከዱላ ላለፈ እንቢ ባይነት… (ለምሳሌ ሌባ) ሽጉጥ አውጥቶ ሲያባርር ያዩ ተማሪዎች፣ በዚያች ቅጽበት እዚያው ክፍል ውስጥ ነበሩ፡፡
ነጩ ጋውን በሰሌዳው አናት ላይ ግማሽ በተመታች ሚስማር ላይ ተሰቀለ፡፡ ዩኒት ሊደሩ ወደ ኤግዚቢቱ እጁን እየቀሰረ…
“ማን ይሄንን ጽሑፍ እንደፃፈ ሳታወጡ…ትምህርት በዚህ ክፍል አይቀጥልም፡፡ አሁን እዚሁ ይሄንን የፃፍክ ግለሰብ ራስህን ካጋለጥክ፣ ግለሰቡ ብቻህን ከዚህ ትምህርት ቤት ትወጣለህ፡፡ ካልሆነ ሁላችሁንም አንድ ላይ…”
ተጠበቀ፤ ማንም መናገር አልቻለም፡፡ ለወትሮው አይኑ ከማህሌት ላይ የማይነቀለው ባዮሎጂ መምህር ወደ ማህሌት አቅጣጫ ለቅጽበት እንኳን አልተመለከተም፡፡ ማህሌት በጠረጴዛው ስር የኤስን እጅ ጭምቅ አደረገችው “ጉዴ ፈላ” ማለቷ ይሁን ወይንም “ከዚህ አውጣኝ” ግልጽ አልሆነለትም፡፡
የተማሪው አፍ ነጭ ሆኗል፡፡ ትምህርት ማለት እውቀት ብቻ ሳይሆን የህልውናም ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት መባረር ማለት ከምድረ ገጽ መሰረዝም ማለት ነው፡፡ አይኖች በጥርጣሬ እርስ በራስ ተያዩ፡፡ ባዮሎጂ አስተማሪው ሌላ ክፍል እንዳልተፃፈበት ሲትሮይን ለሚባለው አስተማሪ ማስረጃ እየጠቀሰ ነው፡፡
“አታወጡም?” ለመጨረሻ ጊዜ ዩኒት ሊደሩ ጠየቀ፡፡ መልስ ጠፋ፡፡ የሰዉ ፊት ሁሉ የጦጣ መስሏል፡፡
“የሁላችሁም የአማርኛ ደብተር ሰብስቡ” አለ ዩኒት ሊደሩ፡፡ ኤስ የአማርኛ ደብተሩ እንደ መጽሐፍ ንባቡ ባይገፋለትም የራሱን ደብተር ከላይ፣ የማህሌትን ከስር አድርጐ አስረከበ፡፡ ማህሌት በጠረጴዛው ላይ ተደፍታ እያለቀሰች ነው፡፡ እያለቀሰች ስለነበረች፣ ሚልኪ በደብተሮቹ ላይ የሰራውን ነገር አልተመለከተችም፡፡
ክፍሉ ተዘግቶ እያንዳንዱ ደብተር በጋውኑ ላይ ከሰፈረው እጅ ጽሑፍ ጋር በጥንቃቄ እየተመሳከረ ተመረመረ፡፡ ዩኒት ሊደሩ፣ ባለ ጥቃቱ ባዮሎጂ አስተማሪ እና ሲትሮይን ለብዙ ፔሬዶች ተማሪው ባለበት ደብተሮቹን ሲያተራምሱ ቆዩ፡፡ በስተመጨረሻ አንድ ደብተር ነጥሮ ወጣ፡፡ ሦስቱም አስተማሪዎች ወንጀለኛው የዚያ እጅ ጽሑፍ ባለቤት መሆኑን መቶ ፐርሰንት ተስማሙበት፡፡ የተማሪው ስም ተነበበ፡፡
ኤስ ስሙ እስኪጠራ አልጠበቀም፡፡ ዝግጁ ሆኖ ነበር፡፡ “አቤት” ብሎ ተነሳ፡፡ የማህሌት ፊት ምን እንደሚመስል ለማየት መጓጓቱ ለእሱ ብቻ ነው የሚታወቀው፡፡ “ኤስ” በዩኒት ሊደሩ እየተገፈተረ ከክፍሉ ወጥቶ ሄደ፡፡
ከሄደ በኋላ ማንም አይቶት አያውቅም፡፡ አንድ አመት ተቀጥቶ ይመለሳል ብለው ጓደኞቹ ቢያስቡም ሳይሆን ቀረ፡፡ ማህሌት ሚስጥሯን ይዛ እንደተብሰለሰለች ትምህርቷን ጨረሰች፡፡ እንዲያውም ማለፊያ ውጤት አግኝታ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት ተቀላቀለች፡፡
Source:- Addis Admass

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s