ያልተነገረ . . .


culturየኛን ሰፈር የማያውቅ ማው; የማያውቅ እጁን ያውጣ፡፡ በጣም ይገርማል ! እስከዛሬ ድረስ የኛን ሰፈር ዝናና ታሪክ ካላወቃችሁ ወይ ካልሰማችሁማ ምኑን ታሪክ አወቃችሁ፡ በቃ አንድ የሆነ ከእውቀታችሁ ላይ የጎደለ ነገር እንዳለ አስቡ፡፡
ንገረን? መንገርማ (ባትጠይቁኝም)እነግራችኋለሁ ነገር ግን ያው “የወሬ ነጋሪ” ማለትም የትረካ ያስከፍላል (እንዴ ሰውን ልብ ብላችሁ ተመልክታችሁት ከሆነ እንደዚች የተበጣጠሰች ገጠመኙን በመፅሃፍ ወይም በፊልም እያወራ ቢዘነስ መስራት ልማድ አደረገው እኮ፡ ታዲያ ወሬ እንደ ስኳር በሚቸረቸርበት ስዓት የሰፈራችንን ዝና በነፃ ልነግራችሁ ፈለጋችሁ ነው? ባይሆን እትየ ዘነቡ ቤት ሁለት ጣሳ ጠላ ስፖነሰር አድርጉኝና እነግራችኋለሁ፡፡(አሪፍ አይዲያ ናት አይደል? በቃ ያዙ…) የኛ ሰፈር በአለም ላይ ከአሜሪካ ቀጥሎ ዴሞክራሲና ቁማር በነፃነት የሚካሄድበት ብቸኛ ሰፈር ነው፡፡ ወደ ሰፈራችን አዲስ የመጣ እንግዳ ሰው ሁሉ በዚህ ነፃነታችን ይገረማል(እንዲውም ጎረቤት ሰፈሮች ከኛ ሰፈር ልምድና ተሞክሮ ወሰደው ጥሩ ውጤት እያመጡ እንደሆነ የሆነ ቴለተቪዥን ጣቢያ ተናግሯል አሉ፡ እኔ ሞቅ ብሎኝ ስለነበር አላስታውሰም፡ ካላመናችሁኝ ግን ቴለተቪዝን ግዙና ተከታተሉ በቅርብ ቀን ይደገም ይሆናል፡፡) በአፍሪቃ ቀዳሚው የእድሜ ጣሪያ ክብረ ወሰንም በኛ ሰፈር ሰዎች እጅ ውስጥ ነው ያለው፡ የተየለሌ እድሜ ያላቸው እነ አቦይ መንግስቱ፣እነ ባላንባራስ ግዛው አና እማሆይ አይቸሽ(እኔ ግን በጣም ስለማከብራቸው “እማሆይ አይቼዎት” ነው የምላቸው፡፡) ሁሉ የኛ ሰፈር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ባላንባራስ ግዛውን የሚደርስባቸው የለም፡፡ እድሜያቸው መቶን ከዘለለ እንደሰነባበተ ቢናገሩም ሰፈራችን ሰዎች ከመቶ ያለፈ ቁጥር ሰለማይችሉ የሚያረጋግጥላቸው አልተገኘም፡፡ አንድ ቀን ከቁማር የሰበሰብኩትን ብር ጠረጴዛ ላይ በትኘ እየቆጠርኩ እያለ እናቴ ምሳ ይዛልኝ ከወደ ጓዳው እየወጣች “ዛሬስ ስንት ብር በላህ? መቶ ይሞላል?” አለችኝ፡፡ የቆጠርኩን ብር አደራጅቼ ወደ ኪሴ እያስገባሁ “መቶ ሰላሳ ብር በልቻለሁ!” አልኳት ፊቴ በደስታ በርቶ፡፡ እናቴ ሞኝህን ፈልግ! በሚል አይነት በከፊል ስቃ “ከመቶ ብር በላይ ደግሞ እንዴት አይነት ብር መጣ? ትልቁ የብር ኖት መጠናችን መቶ ብር አይደል እንዴ?” ብላኝ እርፍ!!(ግን አይገርማችሁም የኛ ኑሮ፡ አንዳንዴ ሳስበው ኑሯችን ራሱ በመቶ ብር ኖት ውስጥ የተቀነበበ ይመስለኛል!!) እና እየውላችሁ የባላንባራስ እድሜም መቶን በመዝለሉ መቶ ላይ ቆመ፡፡ ለነገሩ የባላንባራስ እድሜ እንኳን ለሰፈርተኛው ለአለቃ ጎሹ እንኳ አቅቷቸዋል፡፡ አለቃ ጎሹ በሰፈራችን ውስጥ የታወቁና አንቱ የተባሉ ደብተራ ሲሆኑ የማያውቁት የመድሃኒት ስርና የሰይጣን ዘር የለም፡ስለዚህም ብዙ ሰው ይፈራቸዋል፡፡ አለቃ ከባላንባራስ እድሜ ውጭ ያቃታቸው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ከግቢያቸው በር ላይ ያለው ትልቅ የኮሶ ዛፍ እትየ ዘነቡ ጠላ ቤት በር ላይ ነበር አሉ፡፡ እማሆይ የኋሌ በተስኪያን ሲሄዱ ግራዝማች አንዳርጌ ደግሞ አረቄ ጠጥተው ሲወጡ በተከታታይ ጋኔን አጣሟቸው ከሞቱ በኋላ በአስማት ወስደውት ነው ብሎ አውርቶኛል የአለቃ ወሬ አቀባይ፡፡ ውይ ወሬ ወይ ጉራ!! የአለማችን አንደኛ ጉረኛ ማነው? እርግጠኛ ነኝ ደረጃ መዳቢዎቹ የኛን ሰፈር ካርታ ላይ ካላጡት መጥተው ቢያዩት ያለምንም ድካም (እንደ ቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ)ብቸኛ ተወዳዳሪ አድርገው ጂኒየስ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ ላይ ስሙን ይመዘግቡት ነበር፡፡ በስመ አብ!! መቼም ተሳስቶት “አላውቅም” የሚለው ነገር የለም፡ በዛ ላይ ውሸቱ፡፡ ባለፈው ብላታ ከበደ ቤት የፅጌ ድግስ ላይ ብላታ፣ ባላንባራስ፣እትየ ወርቄ፣ እኔ፣ ሰኒ(ሰናይት ነው ስሟ፡ሰኒ እያልኩ ነው የምጠራት፡፡ በጣም ቆንጆ ናት!!) እና ቤቢ (ሰባት አመቱ ነው) ሆነን ካርታ እየተጫወትን ሳለ የሰፈራችን እውቅ ቀጥቃጭ ጋር ሲያወራ “እንኳን ኢሳያስ አፈወርቂ ማነው ስሙ ይሄ እስራኤል መንግስትም የእኔን ያህል ሁኔታ አያውቅም!! ” ሲል ሰምቼው “የማሌዠያው አውሮፕላን የት እንደተደበቀ ንገረኝ?” ልለው ፈልጌ ሳቄን መቆጣጠር አቅቶኝ ተውኩት፡እኔ ጋር ደግሞ አንዋደድም፡፡ የሰፈራችን ሰዎች ከራዲዮና ቴሌቪዥን በላይ የእሱን ወሬ ያምናሉ፡፡ አንደ ቀን እናቴ እርሱ ባሰራጨው ወሬ ተደናግጣ ሳያት ጊዜ “ሰውየው ውሸታም ነው አትስሚው” አልኳት እንዴት እንደማስረዳት ጨንቆኝ፡፡ “ምኑን ነው የዋሸው?” አለችኝ መልሳ፡፡ እንዴ እማየ! “የእሱን ወሬ ከምትሰሚ ራዲዮ አዳምጭ ወይም ከጎረቤት ቴሌቪዥን ተመልች” አልኳት፡፡ እናቴ በግማሽ ፈገግ እያለች “አየ ልጄ! ለራዲዮኑ የሚያቀብለው ጋኔን አይደል ለእሱስ የሚያቀብለው” ….
እንዴ ስለሰይጣን እያወራሁ ስዓት ሲያልፍብኝ ዝም ትላላችሁ እንዴ? ለማንኛውምይህንን ያህል ከነገርኳችሁ ይበቃል፡፡ ያውም ለሁለት ጣሳ ጠላ? እንዲያውም በዝቷል፡፡ በሉ እኔ ልሂድና ጉሮሮየን ላቀዘወቅዘው እናንተም የነገርኳችሁን አብሰልስሉ(አሪፍ ስቶሪ ነች አይደል? በቃ ስፖንሰር አድርጉኝና አሳትማታለሁ፡፡)
 Moges Bayable©

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s