ሻካራ እጆች


የአንድ ኩባንያ ባለቤት ለደርጅቱ ብቁ የሆነ ሥራ አስኪያጅ ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ላወጣው ማስታወቂያ ባቀረቡት ማስረጃ ተወዳድረው ካለፉት ሦስት ሰዎች መካከል በዕድሜ ትንሽ የሆነውን ለቃለ መጠይቅ ጠራው፡፡
ወጣቱ በተጠራበት ቀን አለባበሱን አሳምሮ መንፈሱንም አንቅቶ ጠበቀ፡፡ የኩባንያው ባለቤት የወጣቱን የትምህርት እና የሥራ ሁኔታ የሚገልጠውን መረጃ አገላብጦ አየው፡፡ የተማረው በሀገሪቱ ውስጥ አንቱ በሚባሉ ት/ቤቶች ነው፡፡ የመጀመርያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን የሠራው እጅግ በጣም ሀብታሞች በሚማሩባቸው ኮሌጆች ውስጥ ነው፡፡ ያገኛቸው ውጤቶች ምርጥ ከሚባሉት ውጤቶች ውስጥ ናቸው፡፡ በየደረጃው ከነበሩ መምህራን እና የትምህርት ባለሞያዎች ሽልማቶችን እና ማበረታቻዎችን አግኝቷል፡፡
የኩባንያው ባለቤት «ይህንን ሁሉ የትምህርት ክፍያ ይከፍልልህ የነበረው አባትህ ነው)» ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም «አይደለም፤ አባቴን በልጅነቴ ነው ያጣሁት» ሲል መለሰለት፡፡ «ኦ ይቅርታ፤ ታድያ ስኮላርሺፕ አግኝተህ ነበር)» አለው፡፡
«እስካሁን በትምህርት ጉዞዬ ስኮላርሺፕ የሚባል አላጋጠመኝም» ብሎ ፈገግ አለ፡፡
«መቼም ከዘመዶችህ አንዱ የተሻለ ገቢ ያለው ሰው መሆን አለበት)» አለና የኩባንያው ባለቤትም ፈገግታውን በፈገግታ መለሰለት፡፡
«እኔ ሀብታም ዘመድ የለኝም፤ ኧረ እንዲያውም ዘመድ ራሱ የለኝም» አለው ወጣቱ፡፡
የኩባንያው ባለቤት እየተገረመ «ታድያ ይህንን በመሰሉ ት/ቤቶች ገብቶ ለመማር እኮ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፤ ማን እየከፈለልህ ነበር የምትማረው)» ሲል በአግራሞት ጠየቀው፡፡
«የምትከፍልልኝ እናቴ ነበረች» አለና ወጣቱ በኩራት መለሰ፡፡
«እናትህ ምን ዓይነት ሥራ ነው የምትሠራው)» አለው ባለቤቱ፡፡
«እናቴ የሰዎችን ልብስ እየሰበሰበች የምታጥብ ሴት ናት» አለው ወጣቱ፡፡
«ልብስ እያጠበች ነው አንተን ይህንን በመሳሰሉ ት/ቤቶች ያስተማረችህ)»
«አዎ»
«አንድ ጊዜ እጅህን ለማዬት እችላለሁ» አለው የኩባንያው ባለቤት፡፡ ወጣቱ እጁን ወደ ባለቤቱ ላከው፡፡ እጁ ከኬክ የለሰለሰ ነበረ፡፡
«ለመሆኑ እናትህን በልብስ አጠባው ረድተሃት ታውቃለህ)»
«አላውቅም»
«ለምን)»
«እናቴ እኔ ምንም ሥራ እንድሠራ አትፈልግም፤ እንድማር፣ እንዳጠና እና እንዳልፍ ብቻ ነው የምትፈልገው፤ ስለዚህ ሥራ ሠርቼ አላውቅም»
«በጣም ጥሩ» አለ የኩባንያው ባለቤት «ቃለ መጠይቁን ነገ እንቀጥላለን፤ አሁን ወደ ቤትህ ሂድና አንድ ነገር አድርግ» አለው፡፡
ወጣቱ እየገረመው «ምን» አለ፡፡
«የእናትህን እጆች እጠብ፤ ከዚያ የሆነውን ነገ ትነግረኛለህ»
በቃለ መጠይቁ የተሻለ ነገር አድርጌያለሁ ብሎ እያሰበ በደስታ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
ቤቱ ገብቶ እናቱን እጇን ለማጠብ ጠየቃት፡፡ አዲስ ነገር ሆነባትና ጠየቀችው፡፡ እርሱም ዛሬ ያጋጠመውን ነገር አጫወታት፡፡
ውኃ እና ሳሙና አቀረበና የእናቱን እጆች ማጠብ ጀመረ፡፡ የተኮራመቱ፤ የተሰነጣጠቁ፤ የቆሳሰሉ፤ የተጠባበሱ፤ እጆች፡፡ የእርሱን እና የእናቱን እጆች እያስተያየ ማልቀስ ጀመረ፡፡ ከሚያጥብበት ውኃ ይልቅ እርሱ የሚያነባው ዕንባ በለጠ፡፡ እነዚህ እጆች እንዲህ የሆኑት እርሱን ለማስተማር መሆኑን አሰበ፡፡ እነዚህ ጠባሶች የእርሱ ጠባሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ቁስሎች የእርሱ ቁስሎች ናቸው፤ እነዚህ እጆች ናቸው ለእርሱ የትምህርት ውጤት መሠረቶቹ፣ እነዚህ እጆች ናቸው እርሱን ለአካዳሚያዊ ውጤት ያበቁት፤ እነዚህ እጆች ናቸው ዛሬ ለቆመበት ታላቅ ደረጃ ያበቁት፡፡
የእናቱን እጆች አጥቦ ሲጨረስ የቀሩትን ልብሶች ሁሉ ከእናቱ ጋር አጠበ፡፡ በዚያች ሌሊት ያ ልጅ ከእናቱ ጋር ለረዥም ሰዓት ሲያወሩ አደሩ፡፡ ነግራው የማታውቀውን ታሪክ ነገረችው፤ ሰምቶት የማያውቀውን ታሪክም ሰማ፡፡
በማግስቱ ወጣቱ ወደ ኩባንያው ባለቤት ዘንድ ሄደ፡፡ የኩባንያው ባለቤት የወጣቱን ዓይኖች ሲያይ የዕንባዎቹን ፈለግ ተመለከተ፡፡ እናም «ትናንት ያደረግከውን እና ያጋጠመህን ልትነግረን ትችላለህ)» ሲል ጠየቀው፡፡
«የእናቴን እጆች አጠብኳቸው፡፡ የእናቴ እጆች እንደዚህ መሆናቸውን አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ነገር ነገረችኝ፤ ልብሶቹንም አብሬያት አጠብኩ» አለው፡፡
«ታድያ ምን ተማርክ)» አለው የኩባንያው ባለቤት፡፡
«ሦስት ነገሮችን ተምሬያለሁ» አለ ወጣቱ፡፡ «መጀመርያ ነገር አድናቆት እና ምስጋናን ተምሬያለሁ፡፡ እናቴ ባትኖር ለእኔም ያንን ሁሉ መከራ ባትቀበል ኖሮ ዛሬ የደረስኩበት ልደርስ አልችልም ነበር፡፡ ስለዚህ እናቴን ምንጊዜም ላመሰግን፤ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ቀድሜ ስሟን ልጠራ፤ ስለ ራሴ ከመናገሬ በፊት ስለ እርሷ ልናገር እንደሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እናቴ ያለፈችበትን እውነተኛው ነገር መረዳት የቻልኩት አብሬያት ሆኜ ሥራዋን ስጋራት ነው፡፡ በሱታፌ ካልሆነ በቀር በነቢብ እና በትምህርት ብቻ የአንድን ነገር ርግጠኛ ጠባይ እና ሁኔታ መረዳት አይቻልም፡፡ ሦስተኛ ደግሞ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ መኖር ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊ ትሥሥርም ወሳኝ መሆኑን አይቻለሁ፡፡» አለው
የኩባንያውም ባለቤት «የምፈልገው ሥራ አስኪያጅ አሁን ተገኘ፡፡ ለእርሱ ሕይወት ሌሎች የከፈሉትን ሰማዕትነት የሚረዳ፤ አብሮ በመሥራት ችግሮችን መቅመስን እና መፍታትን የተማረ፤ የሥራ ግቡ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ያልሆነ ሰው አሁን ተገኘ» አለና ቀጠረው
(remmembered from what I read . . .)

Advertisements

please enter a message

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s